የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስርዓት ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስርዓት ለማስፈን እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የተፋሰስ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስማማው ቁሜ እንዳሉት፥ 90 በመቶ የሚደርሰው የገጸ-ምድር የውሃ መጠን የሚገኘው በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍሎች ነው፡፡ 

40 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በዚሁ አካባቢ ይኖራል ነው ያሉት፡፡

በመካከለኛውና በመካከለኛው ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል ያለው የገጸ ምድር ውሃ ደግሞ 10 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፥ 60 ከመቶ የሚሆነው ህዝብም ይኖርበታል፡፡

በዚህም በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የውሃ ስርጭትና ግኝቱ በተፈጥሮ የተዛባ መሆኑን ነው አቶ አስማማው የተናገሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ የሃገሪቱን የውሃ ሃብት በፍትሃዊነት ማከፋፈልና በፍትሃዊነት አስተካክሎ መምራት ይጠይቃል ብለዋል።

ለዚሀም የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስርዓት ለማስፈን እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በ12 ተፋሰሶች የምትከፈለው ኢትዮጵያ 123 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የገጸ-ምድርና እስከ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የሚደርስ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡


ምንጭ፦ ኢዜአ