ትራምፕ የመረጧቸው ቀጣዩ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ ሹመቱን አለመቀበላቸው ተሰማ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ትራምፕ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪቸው እንዲሆኑ የመረጧቸው ሮበርት ሃዋርድ ሹመቱን እንደማይቀበሉት አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጡረተኛውን ምክትል አድሚራል ሮበርት ሃዋርድን የመረጡት የቀድሞ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪያቸው ነበሩትን ማይክል ፍሊንን ተክተው እንዲሰሩ ነው ተብሏል፡፡

የዋይት ሃውስ ምንጮችን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፥ ሃዋርድ ሹመቱን የማይቀበሉት በቤተሰብ እና በሌላ ምክንያት ነው፡፡

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ግን ሃዋርድ ቦታውን ከያዙ የራሳቸውን ቡድን ይዘው መምጣት ፍላጎት ሳይኖራቸው አይቀርም እያሉ ነው፡፡

የ60 አመቱ ሃዋርድ በትራምፕ አስተዳደር በሙያም ሆነ በግል የሚመቻቸው ቢሆንም ፥ የቀረበላቸውን ሹመት የማይቀበሉት በግል ምክንያቶች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሃዋርድ በአቡ ዳቢ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ኮንትራክተር በሆነው ሎክሂድ ማርቲን ውስጥ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡

ምንጭ፦ቢቢሲ

ተተርጉሞ የተጫነው ፦በእስክንድር ከበደ