ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲሰ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን የነበሩት የሲልቪያ ፓንክረስት ወንድ ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ፓንክረስት ወደ ኢትዮጵያ  የመጡት በ1956 ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ህይወታቸውን በኢትዮጵያ ጥናቶች ላይ ያሳለፉ ሲሆን፥ በአጠቃላይ 400 ጽሑፎችን ለዓለም አቀፍ መጽሔቶች ሲያቀርቡ፣ 22 መጽሓፎችን በትብብር እና 17 መጽሓፎችን በራሳቸው ፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት ፅፈዋል። በበርካታ መፅህፍት ላይም አርትኦት ሰርተዋል።

የአክሱም ሐውልት ከሮም እንዲመለስ ከፍተኛ ንቅናቄ በማድረግም ይታወሳሉ ፕሮፌሰር ፓንክረስት።

በዚህ ስራቸውም በፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለኢትዮጵያ ባደረጉት የጥናት አበርክቶም በእንሊዝ መንግስት የኦ ቢ ኢ ሽልማት አግኝተዋል።

 

የኢፊዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በእኝህ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁም ለባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት፣ ለልጆቻቸው ለሄልን እና አሉላ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን ተመኝተዋል።

 

 

በምህረት አንዱዓለም

android_ads__.jpg