በባቡር ሃዲድ ላይ እየደረሱ ያሉ አደጋዎች አገልግሎቱን እያስተጓጎሉ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተሽከርካሪዎች በባቡር ሃዲድ ላይ እያደረሱ ያለው አደጋ አገልግሎቱን እያስተተጓጎሉብኝ ነው ሲል የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ገለጸ።

ተሽከርካሪዎቹ አጥር ጥሰው ወደ ሃዲዱ በመግባት በመሰረተ ልማቱ ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ባሻገር አገልግሎቱን በማስተጓጎል የሚፈጥሩት ጫና ከአቅሜ በላይ ሆኗል ብሏል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በሚሰጡ 27 ባቡሮች በቀን እስከ 120 ሺህ ተሳፋሪዎችን ያጓጉዛል።

የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተር አቶ አወቀ ሙሉ፥ በተሽከርካሪዎች በሚፈጠሩ አደጋዎች የተነሳ ለደንበኞች በሠዓቱ አገልግሎት ለመስጠት እየተቸገርን ነው ብለዋል።

እንደ ዳሬክተሩ ገለጻ የሚደርሱት አደጋዎች ባቡሩን ከሌሎች ተሽከርካሪዎች ጋር በሚያገናኙ መስመሮች አጥር ጥሰው በመግባት የሚፈጠሩ ናቸው።

ተሽከርካሪ ሃዲድ ውስጥ ገብቶ እስኪወጣ የመስመሩ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ በድርጅቱ ላይ ከሚያደርሰው ኪሳራ ባሻገር የደንበኞች መጉላላት አሳሳቢ እየሆነ ነው ብለዋል አቶ አወቀ።

ባቡሮቹ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በየ15 ደቂቃ ልዩነት፤ በማይበዛባቸው ደግሞ በ20 ደቂቃ የሚደርሱ ሲሆን አደጋ ሲያጋጥም አገልግሎቱ እስከ ሁለት ሠዓት እንደሚቋረጥ ነው የተናገሩት።

በተደጋጋሚ በሚደርሰው አደጋ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ በበራሪ ወረቀቶችና ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች ትምህርት ቢሰጥም ችግሩ አለመቀነሱን ጠቁመዋል።

ባቡሩ የራሱ መስመር ቢኖረውም በመሰረተ ልማቱ ላይ የሚደርሱ አደጋዎችና በአገልግሎቱ ላይ እያስከተሉት ያለው ጫና ከድርጅቱ አቅም በላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

"እየተጎዳ ያለው የአገር ሃብት በመሆኑ ድርጅቱ ብቻውን የሚያመጣው ለውጥ የለም" ያሉት ዳይሬክተሩ አሽከርካሪዎችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የህብረተሰቡን ፍላጎትና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መሰረት በማድረግ አገልግሎቱን ለማዘመን የኤሌክትሮኒክስ ትኬት ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ለመጀመር በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ማሽኖች ተተክለው አሰራሩ እየተፈተሸ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ትኬት ሳይገዙ የሚገቡ ተሳፋሪዎችን ለመቅጣት የወጣው መመሪያ ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ ከ7 ሺህ በላይ ተሳፋሪዎች የተቀጡ ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ትኬቱ ተግባራዊ ሲሆን የትኬት ማጭበርበር ችግሩ እንደሚወገድ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ካሉት 41 ባቡሮች 27ቱ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ቀሪዎቹ በመጠባባቂያነት መያዛቸውን ከትራንዚት አገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ