የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በፍጥነትና በጥራት ለመስራት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቤት ችግርን መፍታት የሚያስችሉ አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ተጨማሪ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ደምሴ ሽቱ።

ሚኒስትር ዴኤታው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተሻለ ቴክኖሎጂና ዲዛይን በፍጥነትና ጥራት ለመስራት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ተቋማት ቤት ገንብተው ለነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያከራዩ የማድረግ ተግባር ሌላው የቅርብ ጊዜ አማራጭ ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑንም አንስተዋል።

በአዲስ አበባ በማህበር ለሚደራጁ በዝቅተኛ የሊዝ ዋጋ መሬት ማዘጋጀት፣ በመዲናዋ እና የክልል ከተሞች ለሪል ስቴት ገንቢዎች መሬትን በስፋት ማቅረብ የሚል አማራጭም ተቀምጧል ነው ያሉት።

ሚኒስትር ዴኤታው የክልሎችን የቤት ችግር ያቀላል የተባለው የማህበራት ቤት ግንባታ በትግበራ ሂደት ውስጥ ያለ መሆኑንና የመሬት ዝግጅትና የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በጥናት ላይ ያሉትም ሆነ በሂደት ላይ የሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በፍጥነት እና በጥራት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ አማራጮችን የሚከታተል ኮማንድ ፖስት ተዘጋጅቶላቸዋል።

የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል ናቸው የተባሉት እነዚህ አሰራሮችና ጥናቶችን በፍጥነት አጠናቆ ወደ ተግባር በማስገባት በከተሞች ያለውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት።

ከ12 አመት በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሀ ግብር ከተጀመረ አንስቶ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች 245 ሺህ ቤቶች ለነዋሪዎች ተላልፈዋል።

ይህም በአማካይ ከ1 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ነው።

እስካሁን ተገንብተው ከተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውጪ በአዲስ አበባ ከ131 ሺህ በላይና በክልሎች ደግሞ ወደ 7 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች በግንባታ ላይ ናቸው።

 

 

በሀይለኢየሱስ ስዩም

 

android_ads__.jpg