ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ እየሰራች መሆኑን ጠ/ሚ ኃይለማርያም ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማሳደግ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥታ ስተሰራ መቆየቷን አስታውቀዋል።

ግንኙነቱን የበለጠ የተሳሰረ ለማድረግ በጋራ የሚሰራበት ማእቀፍ እንዲኖር በተለይም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ማእቀፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ነው ብለዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ያለው አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር በጋራ በመሆን እየሰራች መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

በዚህ ዙሪያም በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ከሚጠቀሱት ሱዳን እና ኬንያ ጋር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሁለትዮሽ ግንኙነት በኩልም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጥሩ የሆነ ደረጃ ላይ ናት ያሉ ሲሆን፥ ጅቡቲ ጋር እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ስትራቴጂያዊ ግንኙነት መኖሩንም ተናግረዋል።

“ከጅቡቲ ጋር ያለን ግንኙነት ከሌሎች ሃገራት ጋር ካለው ወዳጅነት አንድ ደረጃ ከፍ ያለ ነው፤ ከጅቡቲ ጋር ኢኮኖሚያዊ ትርርስ ለመፍጠር ስምምነት ተፈራርመናል” ሲሉም አብራርተዋል።

ስምምነቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜም ከጅቡቲ ጋር ያለው የኢኮኖሚ መስተጋብር ከፍተኛ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከሱዳን እና ከኬንያ ጋር ጋር ያላት ግንኙነት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ያለ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ከደቡብ ሱዳን እና ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነትንም መልካም እና ጥሩ ብለው ጠርተውታል።

ሶማሊያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለች ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም በአሚሶም ጥላ ስር እና ከአሚሶም ውጪ በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱ ሰላም እየተረጋጋ በሚመጣበት ጊዜም ከሶማሊያ ጋር በመሰረተ ልማት ለመገናኘት እንሰራለን ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን ለተፈጠረው ቀውስ እልባት ለመስጠት፥ በቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ አቅጣጫ ይቀመጣልም ብለዋል።

በዚህች አገር ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የበኩሏን እየተወጣች መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 

በምናለ ብርሃኑና ሙለታ መንገሻ

android_ads__.jpg