የፌዴራልና የክልል መንግስታት በተለያዩ ፓርቲዎች ቢመሩ በሁለቱ መንግስታት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስን ህግ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራልና የክልል መንግስታትን በህገ መንግስቱ በጋራ ለመወስን በተሰጣቸው ስልጣኖች ላይ በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ እና የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚመለከት አዲስ የህግ ማእቀፍ ተዘጋጀ።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ስልጣን እና ተግባራትን ለይቶ ባስቀመጠባቸው አንቀፆች ለፌዴራሉም ለክልሉም መንግስት የተሰጠ ተመሳሳይ ስልጣን እና ተግባር አለ።

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 51 የፌዴራል መንግስቱ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና እቅድ የማውጣት እና የማስፈፀም ስልጣን ተሰጥቶታል።

በአንቀፅ 52 መሰረት የክልል መንግስታት የራሳቸውን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና እቅድ የማውጣት ስልጣን ባለቤት ናቸው።

ይህ በህገ መንግስቱ ለሁለቱ መንግስታት በጋራ ከተሰጡ ስልጣኖች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራል ስርዓት ጥናት ተቋም ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አሰፋ ፍስሃ ይናገራሉ።

የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ይህንን ህገ መንግስታዊ ስልጣን በጋራ እና በመመካከር መፈፀም እንዳለባቸው ይታመናል።

እስካሁን ባለው አሰራር ሁለቱ መንግስታት የጋራ ስልጣናቸውን በጋራ እና በምክክር ቢሰሩም አሰራሩ ግን ተለምዷዊ እንጂ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌውን በዝርዝር የሚመለከት የህግ ማእቀፍ አልነበረውም ይላሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የመንግስታት የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከሪያ ዳይሬክተሩ አቶ አስቻለው ተክሌ።

የሀገራትን ልምድ እና ተለምዷዊ አሰራርን መሰረት ያደረገው አሰራርም የፌዴራል እና የክልል መንግስታት በህገ መንግስቱ በጋራ በተሰጣቸው ስልጣን ላይ እኩል የመወሰን አቅም እንዳይኖራቸው ማድረጉን ጥናቶች ያመላክታሉ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር አሰፋ የጋራ በሆነው ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግስቱ የመወሰን ሚና ጎልቶ ይታያል ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የመንግስታቱን ግንኙነት በህግ ማእቀፍ ለመምራት አራት ዓመታትን የወሰደ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቶ የህግ ማእቀፉ ረቂቅ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

የህግ ማእቀፉ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት በህገ መንግስቱ በተሰጣቸው የጋራ ስልጣን ሊኖራቸው የሚገባ ግንኙነትን የሚመለከት ነው።

የፌዴራሉ መንግስት ሀገራዊ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች እቅድን ሲነድፍ፤ የክልል መንግስታትም በተመሳሳይ ለክልላቸው እቅድን ሲያቅዱ የጋራ በሆኑ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲነጋገሩ፣ በተነጋገሩበት ጉዳይ ላይ በእኩል ተሳትፎ እና የመወስን አቅም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ማስቻል የህግ ማዕቀፉ አንድ አላማ ነው።

በህግ ማዕቀፉ ማርቀቅ ሂደት ላይ የተሳተፉት ተባባሪ ፕሮፌሰር አሰፋ፥ ፖለሲው በፌዴራል ስርዓቱ ምሰሶ የሆነ የጋራ ጉዳይ ላይ እኩል መወሰንን ለመተግበር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የህግ ማእቀፉ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ክፍተቶችንም የመሙላት ሚና እንደሚኖረው የፌዴራሊዝም ጉዳዮች ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አንስተዋል።

በምርጫ ውጤት የክልል እና ፌዴራል መንግስታት በተለያዩ ፓርቲዎች ቢመሩ የየራሳቸውን መንግስት በመሰረቱ ፓርቲዎች መካከል ስለሚኖረው ግንኙነትም በፖሊሲ እና በህግ ማእቀፉ ግልፅ አሰራር ተቀምጧል።

አራት ዓመታትን የፈጀው እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን እና በየደረጃው ያሉ የህዘብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት ውይይት የተካሄደበት የህግ ማዕቀፉ በቅርቡ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።

ከህግ ማዕቀፉ መፅደቅ በኋላ አሰራሩን የሚከታተሉ እና የሚቆጣጠሩ ተቋማት የሚቋቋሙም ይሆናል።

ተቋማቱም የፌዴራል እና የክልል መንግስታት በጋራ የሚወሰኑ ጉዳዮችን ከማቅረብ ጀምሮ እስከ ማስወስን እና ተፈፃሚነታቸውን እስከ መከታተል የደረሰ ሚና ይኖራቸዋል።

  

በታሪክ አዱኛ

android_ads__.jpg