የተገባልን ቃል አለመፈፀሙ በስራችን ላይ እንቅፋት ሆኗል - በደቡብ ኦሞ ዞን የተሰማሩ ባለሃብቶች

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ኦሞ ዞን ለሰፋፊ እርሻ ማልሚያ መሬት ቢቀበሉም ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተያይዞ ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ ባለሀብቶች ቅሬታቸውን ገለጹ።

ባለሀብቶቹ ከ1 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሄክታር መሬትን ከ2001 ጀምሮ ሲወስዱ፥ መንግስት በኦሞ ወንዝ መገንባት የጀመረው ድልድይ በ2002 ዓመተ ምህረት ተጠናቆ ለስራቸው ምቹ እንደሚሆንልን ቃል ተገብቶልን ነበር ይላሉ።

በመንግስትና በአልሚዎቹ መካከል የተደረሰው ስምምነትም፥ መንግስት ለስራቸው መቀላጠፍ አስፈላጊ የሆነውን ድልድይ በ2002 ካጠናቀቀ በኋላ፥ የሶስት ዓመት የግብር እፎይታ ጊዜ ለባለሃብቶቹ እንዲኖራቸው የሚስችል መሆኑን ነው የገለፁት፡፡

ሆኖም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው አልሚዎቹ ከመንግስት ጋር በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን እንዲያከናውኑ ወሳኝ የሆነው ደልድይ፥ ከተያዘለት ጊዜ በስድስት ዓመት ዘግይቶ በ2008 ዓመተ ምህረት መጋቢት ወር አጋማሽ ነው የተጠናቀቀው።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ስራቸውን ለማከናወን የሚያስችላቸው መሰረተ ልማት ዘግይቶ ባለፈው ዓመት ቢጠናቀቅም፥ የተወሰነላቸው የሶስት ዓመት የግብር እፎይታ ጊዜም ከ2008 ጀምሮ ሶስት ዓመታትን ከቆየ በኋላ በ2011 ማለቅ ሲገባው በዚህ ዓመት ያልቃል እንደተባሉ ነው የተናገሩት፡፡

በደቡብ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ድጋፍ እና ክትትል ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ደምሰው ባትቸሬ፥ የኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ መጓተቱ፥ በዞኑ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ገልፀዋል።

የሰፋፊ እርሻ አልሚዎቹን የግብር እፎይታ ጥያቄ በቢሮ ደረጃ እንዳልደረሳቸው የጠቀሱት አቶ ደምሰው፥ ጉዳዩን ለማየት ዝግጁ ነን ብለዋል።

ከኦሞ ወንዝ ድልድይ መዘግየት ጋር በተያያዘም ለስራቸው የሚያስፈልጋቸው የብድር አቅርቦት እንዳልተመቻቸላቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መሬቱን በተረከቡበት ጊዜ ድልድዩ ሲጠናቀቅ ብድር እንደሚሰጣቸው ቃል ቢገባም ፥ ድልድዩ በ2008 ዓመተ ምህረት ሲጠናቀቅ ግን ብድሩን እንዳላገኙ ባለሃብቶቹ አንስተዋል።

የልማት ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንና ማስታወቂያ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ ምስጋናው፥ ልማት ባንኩ ብድር ለማቅረብ ያስቀመጠውን ጊዜ ያላከበረው፥ በጋምቤላ ክልል ካጋጠመው የመሬት መደራረብ ጋር ተያይዞ አሰራሩን ለመፈተሽ ሲባል ብድር በማቆሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ባንኩ አሁን አሰራሩን ፈትሾ ስላገባደደ ጉዳዩ እልባት ያገኛል ነው ያሉት አቶ ሃይሉ።

ከ2000 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በደቡብ ኦሞ ዞን ጥጥና የቅባት እህሎችን ለማምረት 77 ሺህ ሄክታር መሬት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ተሰጥቷል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ወደ ምርት የገባው መሬት ከ4 ሺህ 160 ሄክታር እንደማይበልጥ ከደቡብ ክልል የኢንቨስትመንት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለኢንቨስትመንት ግብ አለመሳካት የመልካም አሰተዳደርና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አለመሟላት በምክንያትንት ተጠቅሷል።

አሁን በሀገር አቅፍ ደረጃ በዘርፉ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የተሻለ ውጤትን እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

 

በሰላማዊት ካሳ

android_ads__.jpg