ኢራቅ በየወሩ 1 ሚሊየን በርሚል ያልተጣራ ነዳጅ ለግብፅ ማቅረብ ልትጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራቅ በየወሩ 1 ሚሊየን በርሚል ያልተጣራ ነዳጅ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ለግብፅ ማቅረብ እንደምትጀምር ተነግሯል፡፡

በግብፅ የኢራቅ አምባሳደር ሃቢብ አል-ሳድር፥ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ኢራቅ ቀላል ያልተጣራ ነዳጅ ለግብፅ ማቅረብ ትጀምራለች ነው ያሉት፡፡

ግብ እና ኢራቅ ባለፈው ህዳር ወር በነዳጅ አቅርቦት ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

በተገባው ውል መሰረት ኢራቅ ለግብፅ የምታቀርበው የነዳጅ መጠን እና የክፍያ ሁኔታ እየታየ አቅርቦቱ እንደሚጨምር ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡

የግብፅ ጀኔራል ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን በበኩሉ፥ ኢራቅ የምታቀርበው የነዳጅ መጠን በግብጽ ያለውን የገበያ ፍላጎት ለመሙላት ያስችላል ብሏል፡፡

ኢራቅ እና ግብፅ የነዳጅ አቅርቦት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙት፥ የሳዑዲ ዓረቢያው የነዳጅ ኩባንያ አርማኮ ወደ ግብፅ የሚስገባውን የነዳጅ አቅርቦት ባልታወቀ ሁኔታ በማቋረጡ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ምንጭ፡-en.amwalalghad.com