በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 6ኛው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይናው ፖሊ ጂ ሲ ኤል ኩባንያ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስድስተኛውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ጉድጓድ ቁፋሮ ትናንት በሂላላ - 7 በይፋ ጀምሯል።

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ከተሰማሩት ኩባንያዎች መካከል ጂ ሲ ኤል የተባለው የቻይና ኩባንያ በኦጋዴን ተፋሰስ ካሉብና ሂላላ በተባሉት አካባቢዎች አምስት ጥልቅ ጉድጓድችን ቆፍሯል።

ኩባንያው አሁን ደግሞ ስድስተኛውንና ሂላላ- 7 በሚል የሚጠራውን የጉድጓድ ቁፋሮ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፍጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ላ ይፋን በተገኙበት በይፋ ጀምሯል።

ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ በአገር አቀፍ ደረጃ የተፈጥሮ ጋዝን ከሶስት አመት በኋላ ማውጣት እንደሚጀመር ለኢቢሲ ተናግረዋል።

የሂላላ - 7 ጉድጓድ ቁፋሮ እንደሌሎቹ ቁፋሮዎች ሁሉ ለተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ብቻ ሳይሆን የነዳጅ ዘይት ፍለጋንም የሚያካትት ልዩ ቁፋሮ መሆኑንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ላ ይፋን በበኩላቸው በኢትዮጵያና በቻይና የተጀመሩ የሁለትዮሽ የትብብር ማዕቀፎች ተጠናክረው ይቀጥለሉ ብለዋል።

መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሁለቱን አገራት ትስስር የሚያጎለብቱ መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት።

የሂላላ-7 የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ጉድጓድ ቁፋሮ በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

ሚኒስትሩና አምባሳደሩ ቁፋሯቸው የተጠናቀቁ የካሉብ ጉድጓዶችን ጎብኝተዋል።

ካሉብ፣ ሂላላና ገናሌ ተብለው በሚጠሩ ቦታዎች 4 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ኪዩ ቢክ ፊት የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳለ ተረጋግጧል።

በአካባቢው የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ በ1970ዎቹ መረጋገጡ የሚታወስ ነው።

ፖሊ ጂ ሲ ኤል የቻይናው ፖሊ ግሩፕ ኮርፖሬሽን እና የሆንግ ኮንጉ የግል ኩባንያ ጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ ጥምረት ነው።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ለመፈለግ በ2013 ነበር ከመንግስት ጋር ስምምነት የተፈራረመው።

በካሉብና በሂላላ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በ25 ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ነው ፖሊ ጂ ሲ ኤል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተስማማው።

 

 

 android_ads__.jpg