"የኛ" በሴቶች የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢመርጅ ማንጎ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ በወጣት ሴቶች ዙሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚሰራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል "የኛ" የተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም የሚያዘጋጀው ድርጅት ኢመርጅ ማንጎ ገለፀ፡፡

"የኛ" በወጣት ሴቶች ዙሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣትን ታሳቢ አድርጎ የሚሰራ የሬዲዮ ፕሮግራም ነው።

የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ እንደገለጹት፥ "የኛ" ፕሮግራም በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ ተደርጎ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል፡፡

በዚህም በወጣት ሴቶች ዙሪያ ያሉ አመለካከቶች፣ እምነቶች እና ምግባሮች ላይ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ እና ወጣት ሴቶች ለማህበረሰባቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ታቅዷል ነው ያሉት ወይዘሮ ሰሎሜ፡፡

"የኛ" ሥራውን ከጀመረ አንስቶ በአጋርነት ሲሰሩ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው የእንግሊዝ ዓለም ዓቀፍ የልማት ድርጅት ትብብሩን ማቋረጡን ባለፈው ዓርብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ድርጅቱ ውሳኔውን የሚያከብር መሆኑንና በሴቶች ዙሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የተጀመረው ሥራ ግን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በቀጣይም የታቀዱ ሥራዎች ሳይሰተጓጎሉ እንደሚቀጥሉና ለዚህም ፍላጎቱ ካላቸው የአገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የእንግሊዝ አለም አቀፍ የልማት ድርጅት ከ2015 እስከ 2018 ድረስ የሚቆይ የ11 ነጥብ 8 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ ለማድረግ አቅዶ እንደነበር የሚታወስ ነው። 

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ

 

android_ads__.jpg