የባህል ወጌሻዎች ስልጠና ሊሰጣቸው ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቂ እውቀትና ልምድ የሌላቸው የባህል ወጌሻዎች ስልጠና ሊሰጣቸው ነው።

ስልጠናው በህብረተሰቡ ውስጥ ትክክለኛ አገልግሎት የሚሰጡ የባህል ወጌሻዎችን በመለየት ተመዝግበው እንዲሰሩ እውቅናና ፍቃድ ለመስጠትም የሚያግዝ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ፥ በእውቀት ማነስ ምክንያት የሚፈጠረውን ስህተት ለመቀነስ የመገጣጠሚያ ቀዶ ህክምና ትምህርት ክፍል
በወጌሻ ስራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ የአጥንት ህክምና ማህበር ጋር በመተባበር የሚሰጠው ስልጠና ህክምና ከመሰጠቱ በፊት ባሉ ጉዳዮች፣ በህክምና ወቅት መደረግ ስላለበት ጥንቃቄና ትኩረት ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች እንዲሁም ከህክምና በኋላ ሊደረጉ ስለሚገቡ እንክብካቤዎች ግንዛቤ መስጠት የሚያስችል ነው።

ማህበሩ እና ሆስፒታሉ ስልጠናውን መስጠት የሚቻለው በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ትክክለኛ የወጌሻ ህክምና እየሰጡ የሚገኙ ባለሙያዎችን ለይቶ መመዝገብ ሲቻል መሆኑን ገልፀዋል።

ትክክለኛ የወጌሻ አገልግሎት እየሰጡ ለመሆናቸው ምስክርነቱን ሊሰጡላቸው የሚችሉ ባለሙያዎችን የመመዝገብ ስራ እንዲከናወን መመሪያ ተዘጋጅቶ ለክልሎች መላኩን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገልጿል።

በባለስልጣኑ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ዳዊት ዲቃሶ እንዳሉት ምዝገባው ሲጠናቀቅ በየዘርፉ የሚመዘገቡት የባህል ህክምና ባለሙያዎች ፍቃድ ተሰጥቷቸው የመንግስትን ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን የሚያስችል አሰራር ለመተግበር ያግዛል።

በዚህም ከዘመናዊ የህክምና ባለሙያው ይልቅ ለህብረተሰቡ ቅርበት ያላቸው እነዚህ ወጌሻዎችም ስራቸውን ይበልጥ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲሰሩ እድል ያገኛሉ ተብሏል።

 

በትዕግስት ስለሺ