ዶክተር ወርቅነህ በፀጥታው ምክር ቤት ተገኝተው ለዓለም ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ ኢትዮጵያ እንደምትሰራ አረጋገጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኒው ዮርክ የሚገኙት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ትናንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተገኙበት የመጀመሪያቸውን የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ተሳትፎ አድርገዋል።

በዓለም ሰላም ማስጠበቅ እና ግጭት መከላከል ላይ አተኩሮ በተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ አዲስ የተመረጡት የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም በዋና ፀሃፊነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

ዶክተር ወርቅነህ በምክር ቤቱ ንግግራቸው ላይ የቀድሞ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

በተለይም የፓሪሱ የዓየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንዲፈረም እና የ2030 የልማት አጀንዳ ተዘጋጅቶ እንዲፀድቅ ያበረከቱት አስተዋፅኦን በዋቢነት አንስተዋል። 

ባን ኪሙንን የተኩት አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዓለም ዙሪያ መፍትሄ የሚፈልጉ ግጭቶች ባሉበት ሁኔታ መምጣታቸውንም ተናግረዋል። 

በአፍሪካ ግጭትን ለመከላከል እና ለማስቆም እየሰራች ያለችው ኢትዮጵያ ለእኝህ አዲስ ዋና ፀሃፊ ድጋፏን እንደምታደረግም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያረጋገጡት። 

ዋና ፀሃፊው በተመድ እና በአፍሪካ ህብረት መካከል ከዚህ ቀደም የተፈጠረውን ጠንካራ ግኑኝነት ያስቀጥሉታል የሚል ተስፋ እንዳለቸው እና በቅርቡም አዲስ አበባ በሚካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው ለዚህ እንደሚያግዛቸው ነው ያመለከቱት። 

ዶክተር ወርቅነህ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ተወያይተዋል። 

በተመድ ዋና ፅህፈት ቤት ባደረጉት ውይይት ላይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ነው የተነጋገሩት።

workneh_and_guterez.jpg

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኒውዮርኩ ስብሰባ ጎን ለጎን ከጣሊያኑ አቻቸው አንጀሊኖ አልፋኖ እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም ውይይት አድርገዋል።

 

 

android_ads__.jpg