ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ከ267 ሚሊየን ብር በላይ እንዲመዘበር አድርገዋል የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ከ267 ሚሊየን ብር በላይ እንዲመዘበር አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ሳሙኤል ግርማና በለጠ ዋቅቤካ የተባሉት ተጠርጣሪዎች በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የፋይናንስ የስራ ሂደትና የብድር ደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር የስራ ሂደት ዳይሬክተሮች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ ከባንኩ እውቅናና ፍቃድ ውጪ በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሪሲቨብል ኤክስፖርት ሴትልመንት የሚል አካውንት በመክፈት፥ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር ከ267 ሚሊየን 675 ሺህ ብር በላይ ባንኩ እንዲመዘበር አድርገዋል በሚል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መንግስታዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ተጠርጣሪዎቹን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ትላንት አቅርቧቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ እና መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን ተቃውሞና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት፥ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ጥር 3 2009 ከሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

 

በበላይ ተስፋዬ