በአዋሽ ተፋሰስ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ መከላከል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን በተፋሰሱ ተደጋጋሚ ችግር የሚያስከትለውን የጎርፍ አደጋ መከላከል የሚያስችል ጥናት ማካሄድ ጀምሬያለሁ አለ።

ከከፍተኛ የመሬት አቀማመጥ ቁልቁል የሚጓዘው የአዋሽ ወንዝ ወደ መካከለኛውና ታችኛው የተፋሰሱ ክፍል ሲደርስ ለጥ ያለ ሜዳማ መልክዓ ምድር ላይ ያርፋል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ 71 በመቶ የሚሆነውን የተፋሰሱን ይዞታ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ አድርጎታል።

በጎርፉ ምክንያትም ተፋሰሱን ተከትለው ኑሯቸውን በመሰረቱ ነዋሪዎች ላይ ተደጋጋሚ አደጋ ሲከሰት ይስተዋላል።

የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣንም ይህን መሰሉን አደጋ ለመከላከል ተደጋጋሚ የጎርፍ መከላከል ዱካ ግንባታና ጥገና ያደርጋል።

በባለስልጣኑ የተቀናጀ የተፋሰስና ወንዝ አመራር ቡድን መሪ አቶ ሃይሌ ገረሱ፥ በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ጥናት መጀመሩን ይናገራሉ።

ጥናቱ ጎርፍ ሊከሰት የሚችልባቸውን አካባቢዎች ቀድሞ በመለየት ማመላከትና አደጋ ቢከሰት በምን መልኩ መከላከል እንደሚቻል የሚያመላክት መሆኑንም ተናግረዋል።

በፌደራል ዲዛይን ኢንተርፕራይዝ በኩል የሚካሄደው ጥናት ከወዲሁ ተጀምሯል።

ጥናቱ ለጎርፍ አደጋው መፍትሄ ከመስጠት ባለፈ የአዋሽን ውሃ ለሚጠቀሙትም በቂ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ የተፋሰስ ባለስልጣኑ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ግዛው ገልጸዋል።

ከዚህ ባላፈም የአርብቶ አደሩን እንስሳት ታሳቢ ያደረገ የጎርፍ መከላከያ መንገድ እንዲኖር ያስችላልም ነው ያሉት፡፡

በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ እቅድ የተያዘለት ጥናት በ26 ሚሊየን ብር የሚካሄድ ነው።

 

 

በሰላማዊት ካሳ