በአመራሮች ላይ ከተሰጠው አስተያየት በመነሳት የስራ ምደባቸው ላይ ውሳኔ ይተላለፋል- ከንቲባ ድሪባ ኩማ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በስራ ላይ ያሉም ሆነ አዲስ አመራሮች በህዝብ የተሰጠባቸውን አስተያየት መሰረት በማድረግ የስራ ምደባቸው ላይ ውሳኔ እንደሚተላለፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስታወቁ።

ከንቲባው በአስሩም ክፈለ ከተሞችና በሁሉም ወረዳዎች በተካሄደው የጥልቅ ተሀድሶ መድረክ ፋይዳ ላይ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በመድረኮቹ ላይ ህዝቡ ጉድለት እንዳለባቸው ያነሳባቸው ነባርም ሆነ አዲስ አመራሮች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በሌሎች አመራሮችም ላይ የህዝቡ አስተያየት መሰረት በማድረግ የስራ ምደባቸውን የማጽደቅ ስራ ይከናወናልም ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፥ “እስካሁን በነበረው አመራሮችን የማስተቸት ስራ ውጤት ያስገኘ ነው፤ ከመልካም አስተዳደር አንጻር ችግር ያለባቸውን አመራሮችም ለመለየት ያስቻለ ነው” ብለዋል።

ከንቲባው ህብረተሰቡ በነጻነት በአመራሩ ላይ ሀሳቡን ሰንዝሯል ያለሉ ሲሆን፥ ሹመት የተሰጣቸውን አመራሮች ለህዝቡ ስናቀርብ ህዝቡ ጥያቄ ያቀረበባቸው አመራሮች አሉ ብለዋል።

ከህዝብ የተገኘውን ሃሳብ መነሻ በማድረግ መረጃ የቀረበባቸውን አመራሮች መልሰን የምናያቸው ይሆናል ሲሉም ከንቲባ ድሪባ አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በቂ ማስረጃ በተገኘባቸው ነባርም ይሁን አዲስ በአመራሮች ላይ አስፈላጊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

አሁንም ቢሆን በከተማ፣ ክፍለ ከተማ እና በወረዳ የሚደረጉ ውይይቶች ይቀጥላሉ ያሉት ከንቲባው፥ ከህዝቡ የሚነሱ አስተያየቶች ላይ ተመርኩዘን ጥሩ ናቸው የተባሉ አመራሮች ስንት ናቸው የሚለውን እንለያለን ብለዋል።

እንዲሁም ችግር አለባቸው የተባሉትን በመለየት የቀረበባቸውን ማስረጃ በመመርመር ችግር እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው የመለየት ስራ ይከናወላል ሲሉም አብራርተዋል።

እነዚህን ካጣራን በኋላ ከ15 እስከ 20 ባሉ ቀናት ውስጥ የማስተካከል እርምጃ ወደ መውሰዱ ስራ እንሸጋገራለን ሱሉም ከንቲuባ ድሪባ ኩማ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በከተማዋ በክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የተካሄዱት የተሀድሶ መድረኮች ህዝብን በቀጥታ ወደሚያገለግለው የፖሊሲና ስትራቴጂ ፈጻሚ ወረዷል።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ መምህራን፣ ሴቶች እንዲሁም ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግስት ጋር በስፋት ተወያይተዋል።

ውይይቱ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ተካሂዷል።

አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችና አመራሮች በጋራ እየመከሩ ነው።

በምክክሩ ላይም ሰራተኛው ምን ያህል አገልግሎት አሰጣጡ ህዝበን ያረካ ነበር? ፤ ምን ይጎድላል እስከሚለው ድረስ ግምገማ ይካሄዳል።

ከዚህ በኋላ ከተማ አሰተዳደሩ በተለይ ህዝብ ቅሬታ በሚያሰማባቸው ተቋማት አገልግሎቴን አስተካክላሁ ብሏል።


በዳዊት በጋሻው