የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን ህጋዊ ማድረግ የሚያስችለው መመሪያ ለአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ሊቀርብ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን በህጋዊ መስመር እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ በያዝነው ወር ለአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ እንደሚቀርብ የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከሰራተኞቹ ጋር በመንግስት የጥልቅ ተሃድሶ ዙሪያ ባደረገው ውይይት፥ በከተማዋ ባለው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተወያይቷል።

በውይይቱ አላግባብ የሚደረግ የንግድ ምዝገባ፣ ለማይገባው ነጋዴ የንግድ ፍቃድ እና እድሳት ማድረግ፣ ያለ አድራሻ መነገድ፣ ህገ ወጥ እና የጎዳና ላይ ንግድ በከተማዋ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው ተብለዋል።

የጎዳና ላይ የንግድ እንቅስቃሴም በዋናነት የዘርፉ ችግር መሆኑ ተነስቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ፥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን በህጋዊ መስመር ለማሰማራት የሚያስችል መመሪያ ለከተማዋ ካቢኔ በዚህ ወር ይቀርባል ብለዋል።

መመሪያው ነጋዴዎቹ የሚሰሩበትን ቦታ፣ ሰዓት እና ቀን ያካተተ ሲሆን ደንብም ይዘጋጅለታል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም መመሪያው ነጋዴዎቹን ህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚከታቸው አስረድተዋል።

መመሪያው ለከተማዋ ካቢኔ ቀርቦ ከፀደቀ በኋላም ደንብ ተዘጋጅቶለት የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን የመመዝገብ ስራ ይሰራል ተብሏል።

ይህ መሆኑ ደግሞ በከተማዋ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ንግድ እና ገበያ ላይ የሚቀርቡ ለህብረተሰቡ ጠንቅ የሆኑ ሸቀጦችን ግብይት እንደሚያስቀር ታምኖበታል።

 

 

 

በዳዊት በጋሻው