በደቡብ ወሎ ዞን በተሽከርካሪ አደጋ የ15 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን ከኩታበር ከተማ ወደ መስቀላ የገጠር ቀበሌ ይጓዘ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተገልብጦ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኮማንደር ሰይድ ሙሔ እንዳሉት፥ በአደጋው ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ በ18 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።

አደጋው የደረሰው የሰሌዳ ቁጥሩ "ኮድ 3 – 07218 አማ" የሆነ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከኩታበር 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው መስቀላ የገጠር ቀበሌ ገበያ ተሳፋሪዎችን ጭኖ በመጓዝ ላይ ሳለ ነበር።

ተሸከርካሪው 67 ሜትር ርዝመት ባለው ገደል ውስጥ ገብቶ መገልበጡንም ኮማንደር ሰይድ ተናግረዋል፡፡

አደጋው ሲከሰት 15 ሰዎች ሕይወታቸው ወዲያውኑ ሲያልፍ አሽከርካሪውን ጨምሮ በስድስት ሰዎች ላይ ከባድና በ12ቱ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱንም ነው የተናገሩት፡፡

ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ተሳፋሪዎች ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተወስደው ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ሲሆን፣ ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ኮማንደሩ አመልክተዋል፡፡

የአደጋው መንስኤ በምርመራ ላይ ቢሆንም የተሽከርካሪው መሪ መበላሸት ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሱ የመጫን አቅሙ 24 ሰዎችን ብቻ ቢሆንም አደጋው በደረሰበት ወቅት 33 ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበር ኮማንደሩ ጠቁመዋል፡፡

የትራፊክ ፖሊስ በቅርብ በማይገኝባቸው የገጠር ቀበሌዎች፥ ሕዝቡ ተሸከርካሪው ከተፈቀደለት በላይ እንዳይጭን በመቆጣጠር በትራፊክ አደጋ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንዲከላከል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡