ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኛትን የባቡር መስመር አስመረቀች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ጅቡቲን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘውና በጅቡቲ በኩል የተዘረጋው የባቡር መስመር ዛሬ በይፋ ተመረቀ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የጅቡቲውን ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌን ጨምሮ፥ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች የአካባቢው ሃገራት ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡

ሁለቱን ሃገራት በባቡር ለማስተሳሰር የተዘረጋው መስመር ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ድረስ 752 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናል።

ኢትዮጵያ የገነባችው 656 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ መመረቁ ይታወሳል።

የባቡር መስመሩን ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ነበር ግንባታውን ያከናወነችው።

በወቅቱ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ እንዲሁም የቶጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፋዩሪ ኦሲዙማ ተገኝተው መርቀውታል።

ዛሬ በይፋ የተመረቀው የባቡር መስመር በጅቡቲ መንግሥት በኩል የተገነባውና 104 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ምርትን የተሳለጠ ለማድረግ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

የባቡር መስመሩ የገቢ ምርትን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት ይወስድ የነበረውን የአራት ቀናት ጉዞ ወደ 13 ሰዓታት ዝቅ የሚያደርግ ነው።