በድንበር አካባቢዎች ህዝቡ የኦነግ እና መሰል የጥፋት ሃይሎችን በመጠቆም ለሰላሙ ዘብ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህዝቡን ያሳተፈ የፀጥታ ቁጥጥር በድንበር አካባቢ የሚገኙ የቦረና ዞን ነዋሪዎች ከስጋት ተላቀው ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ እንዳስቻላቸው ተነግሯል።

በስፍራው ቅኝት ያደረገው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባልደረባ፥ ቀደም ሲል የኬንያን ድንበር አቋርጠው ወደ ሃገር ውሰጥ ይገቡ የነበሩ የጥፋት ሃይሎችን በጋራ ለመቆጣጠር በተሰራው ስራ ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን ተመልክቷል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ሰባት የአሸባሪው ኦነግ አባላትን ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፥ ከዚህ ቀደም አከባባቢው የአሸባሪው ኦነግ አባላትና ሌሎች የጥፋት ሃይሎች ድንበው አቋርጠው ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ጥረት የሚያደርጉበት አከባቢ በመሆኑ ህዝቡ በስጋት ያሳልፍ ነበር።

እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ወደ ሀገር ገብተው መንገደኛውም ላይ ሆነ ነዋሪው ላይ የዝርፊያና መሰል ተግባር ፈጽመው ይወጡ ነበር ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ ።

የጥፋት ኃሎች በየወቅቱ የሚያዙና እርምጃ የሚወሰድባቸው ቢሆንም የነዋሪውን ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ አልቀረፈውም ነበር፡፡

አሁን ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ለውጦች እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት ዞኑ የድንበር አዋሳኝ እንደመሆኑ ለዚህ ችግር ቢጋለጥም፥ ሁሉም ነዋሪ ከጸጥታው ሀይልና ከሚሊሻ አባላት ጋር በመሆን የተጠናከረ የጥበቃ ስራ እንዲሰራ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ስርዓት ተዘርግቷል፤ በዚህም ለውጥ መጥቷል፡፡

ስርዓቱ ነዋሪዎች በአከባቢያቸውም ሆነ በድንበር ላይ ፀጉረ-ልውጥ ሰው ሲያዩ ማንነቱን እንዲጠይቁና ከተጠራጠሩም ለፀጥታ አባላት እንዲያሳውቁ የሚያስችል ነው ።

የተቀናጀ የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ የማስጠበቅ ስራን ሁሉም በሃላፊነትና በባለቤትነት እንደሚሰሩት ነው ነዋሪዎቹ የገለፁት፡፡

የዞኑ አስተዳደርም በሰራቸው ስራዎች በሁለት ወር ውስጥ ሰባት የአሸባሪው ኦነግ አባላት በኡጋንዳ ኬንያን አቋርጠው ሞያሌ እና ደንቢ ዶሎ ላይ ጥፋት ከመፈጸማቸው በፊት በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

የቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሊበን አሬሮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ እንዲህ አይነት ችግሮችን ከውጪም ሆነ ከውስጥ የማጥራት ስራ እየተሰራ ነው።

ስራው ህብረተሰቡን ያሳተፈ በመሆኑ በተጨባጭ ለውጦች የተመዘገቡ ሲሆን፥ ሰላማዊ እንቅሰቃሴ እየታየ ነው ብለዋል አስተዳዳሪው።

በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ ላይ ከህዝቡ ጋር ውይይት እንደሚደረግ ያነሱት የዞኑ አስተዳዳሪ፥ ለሚነሱ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አስችሏል ነው ያሉት።

በተለይ አሁን እየተሰራበት ያለው ህዘብን ያሳተፈ የፀጥታ ስርዓት፥ ሁሉም ሰው አምኖ እንዲቀበለው ከማድረግ ጀምሮ ወደ ተግባር በመግባት ውጤቱን ማየት ተችሏል።

ባለፈው የተፈጠረውን ሁከት በማረጋጋት ረገድም ኮማንድ ፖስቱ ትልቁን ሚና ሲወጣ ህብረተሰቡም የዚሁ ተግባር ተባባሪ ሆኗል።

አሁን የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ በመቀጠል የመጣውን አስተማማኝ ሰላም ወደ ልማት የመቀየር ስራም ቀጥሏል ነው ያሉት አቶ ሊበን።

ነዋሪዎቹም በተሰራው የተቀናጀ ስራ በመጣው ውጤት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።

ለከብቶቻቸው መኖ በሰላም ማዘጋጀት የቻሉ ሲሆን፥ ቀደሞ ከነበረባቸው ስጋት ተላቀው በሰላም ወጥተው መግባት እንደቻሉ ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በተጨማሪም የድንበር አከባቢ መረጋጋት በመኖሩ ፀጥታውን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ፊታቸውን ወደ ተቀናጁ የልማት ስራዎች ማዞራቸው ተገልጿል፡፡

 

በሀይለኢየሱስ ስዩም