ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ጥቅም የሚወስነው ህግ የመጀመሪያው ረቂቅ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ጥቅም የሚወስነው ህግ የመጀመሪያው ረቂቅ ተዘጋጅቷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ በረቂቁ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ተወያይተውበት ይጸድቃል ብለዋል።

ጉዳዩ ህገ መንግስታዊ ስለሆነ መውጣቱ አከራካሪ አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ህጉ በበሰለ ሁኔታ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን ጥቅም በሚያሳይ መልኩ መውጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

ረቂቅ ህጉ በቀጣይ ከህዝቡ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ይደረግበታልም ብለዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት

ከአመታዊ አጠቃላይ ምርቷ 40 በመቶውን ለኢንቨስትመንት በምታውል ሀገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢኖር አይደንቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዳከማቹ የሚነገርላቸው እነ ቻይና እና ደቡብ ኮርያ በኢትዮጵያ የእድገት ደረጃ ላይ በነበሩበት ወቅት የሴቶቻቸውን ጸጉር ለውጭ ምንዛሬ ሲሉ እንደሸጡ አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ የቀነሰው የምትልካቸው የግብርና ምርቶች መጠንም ጨምሮ ነው።

ምክንያቱም የአለም የግብርና ምርቶች ዋጋ ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጭ ነው፤ ኢትዮጵያ ግን የሚጠበቅባትን የምርት ጭማሬ አድርጋለች፤ ስለዚህም ነገሩን በትክክለኛው መነጽር ማየት ይገባል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም።

የአምራች ኢንዱስትሪው አሁንም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንና እንደ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉትን ማስፋፋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል ።

በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከፍ ለማድረግ የባህረ ሰላጤው ሀገራትን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ወዳጆች ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በማድረግ ረገድ ባለፈው አመት ስኬታማ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝቷ እንዲያድግ ተመኗን ትቀንስ የሚሉ ምሁራን ሙሉ ለሙሉ ተሳስተዋል ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም ይህን ማድረግ በጥቂቱም ቢሆን የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ስለሚያሳድግ ነው ብለዋል ።

ሆኖም የውጭ ምንዛሬ ተመን እንዲቀንስ ቢደረግ ግን ከውጭ የሚገቡ እቃዎች የሀገር ውስጥ ዋጋቸው ከፍ ስለሚል የሀገር ውስጥ ባለሀብቱን ይጎዳዋል፤ ስለዚህ ምርጫው ተመኑን አለመቀነስ ይሆናል የሚል ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በሁለቱ ጽንሰ ሀሳቦች መካከል አማካኝ የሆኑ ጉዳዮች ከተገኙ ግን መንግስት ሊያየው እንደሚችል ነው የተናገሩት።

የስራ እድል ፈጠራ

መንግስት አሁን ላይ የተከለሰውን የወጣቶች ፓኬጅ ለክልሎች እንዲተገብሩ ልኮላቸዋል።

ፓኬጁ ወጣቱ መንግስት በመደበው ገንዘብ ተገቢውን ስራ እንዲያከናውን ያደርጋል፤ ወጣቱም በጉዳዩ ላይ አምኖበት እንዲሰራ ይጠበቃል ብለዋል አቶ ኃይለማርያም።

ከዚህ ቀደም መንግስት ለስራ ፈጠራ ብሎ ብዙ ገንዘብ ቢመድብም የማሳመን ስራ ባለመከናወኑ የተሳካላቸው ቢኖሩም ያልተከካላቸውም ጥቂት አይደሉም ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቶች ለሚገቡበት ስራ ድጋፍ እንዲሁም የፕሮጀክት ቀረጻ ያስፈልጋቸዋል፤ የገንዘብ ብክነት እንዳይኖርም አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል።

ሰፋፊ እርሻዎች

ከሰፋፊ እርሻ ባለሀብቶች ጋር በተያያዘ መንግስት ያጋጠመው የፖሊሲ ሳይሆን የአፈጻጸም ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ዘርፍ ላይ 46 ባለሀብቶች ብቻ በጥሩ አፈጻጸም የቀጠሉ መሆናቸውን አንስተው፥ 220 ባለሀብቶች ግን መንግስት ዘርፉ ላይ ስኬታማ እንዲሆኑ ያቀረበላቸውን ድጋፍ ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግስት ቀድሞ የነበረው የግብርና ኢንቨስትመንትና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲን በመተካት በዘርፉ ላይ ሰፊ ቁጥጥርን የሚያደርግ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለስልጣንን አቋቁሟል።

ባለስልጣኑ የሙያ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፥ የባንክ ብድራቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት መሆኑን ይከታተላል ብለዋል።

ባለሃብቶች ከቀረጥ ነፃ ያስገቧቸውን ሀብቶች በአግባቡ እየተጠቀሙባቸው መሆኑንም ይቆጣጠራል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ለመንግስት ሰራተኞች በዚህ አመት አጋማሽ ይደረጋል የተባለው የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ጉዳይም በጥር ወር መጨረሻ ምላሽ እንደመኪያገኝ ይጠበቃል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም።

 

በካሳዬ ወልዴ

 

android_ads__.jpg