በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ በመሳተፍ መረጃ እስከቀረበ ድረስ መንግስት ማንንም አይምርም - ጠ/ሚ ኃይለማርያም

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተሳተፉ አመራሮች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ መንግስት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህ መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም፥ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ለመታገል እና በዚህ ተግባር ላይ ተሳትፈው የተገኙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ስር ራሱን የቻለ የምርመራ ቢሮ መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።

በመግለጫቸው ላይ መንግስት የጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ህዝብን ለማገልገል ቁርጠኛ የሆኑ አመራሮችን ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ ያስቻለ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በእንቅስቃሴው የሙስና ችግር አለባቸው ተብለው የተጠቆሙ አመራሮች ላይ የተጠናከረ ምርመራ እንደሚካሄድ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ ማስረጃ እስከቀረበ ድረስ መንግስት ማንንም አይምርም ብለዋል።

በጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች በተደረጉ ግምገማ እና ውይይቶች በርካታ ችግሮች ተነስተዋል፤  በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ባለጉዳይን በአግባቡ ያለማስተናገድ፣ ቆጠሮ ሰጥቶ መስራት እንዲሁም በመንግስት ወጪ የተለያዩ የውጭ ሀገር ጉዞዎችን ማብዛት፣ በቢሮ ውስጥ አለመገኘትና በተወሰነ መልኩም ቢሆን የመንግስት ስልጣንን ተገን አድርጎ ሀብት የማከማቸት እና ሙስና እና ስርቆትም ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው ታይቷል ብለዋል።

መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ መድረኮቹ የተገኙ ግብአቶችን ተጠቅሞ በሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ተጠርጥረው በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸውን ለይቶ የአመራር ለውጥ ማድረጉንም አብራርተዋል።

በተገኙ ማስረጃዎች በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸውን አካላት አስፈላጊው አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየተደረገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም፥ በግምገማ መድረኮች እና በህዝብ ጥቆማ በተገኙ ማስረጃዎች መሰረት የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ለዚህም ተቋማዊ አቅም የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

ስልጣናቸውን ተጠቅመው የህዝብ ሀብትን የመዘበሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ እና ህዝቡ ጥቆማ እንዲሰጥ የዲሞክራሲ ማዕከል የተሰኘ ተቋም መቋቋሙን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል አሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሀገሪቱ ላይ ያደረሰው አሉታዊ ተፅዕኖ አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም፥ አዋጁ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ሰላምና አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም ብለዋል።

ጉዳት በጥቂቱም ቢሆን የታየው በአገልግሎት ዘርፍ በተለይም በቱሪዝም ላይ ነው፤ አዋጁ በዘርፉ የሚኖረውን ተፅዕኖ  ለማወቅም ጥናት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይቀጥል ወይስ ይነሳል የሚለውን ለመወሰን የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት መቀጠሉን ማረጋገጥ እና ህዝቡ አዋጁ ላይ ያለውን ሀሳብ ማድመጥ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት የሚያስችል መሪ እቅድ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አማካኝነት መዘጋጀቱን በመግለጫቸው አመላክተዋል።

በግብፅ የሚገኙ ተቋማት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብተው ሀገሪቱን ለማተራመስ ባደረጉት እንቅስቃሴ ዙሪያ የኢፌዴሪ መንግስት በኢትዮጵያ የአገሪቱን አምባሳደር ጠርቶ ማብራሪያ መጠየቁን እና ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ ኤል ሲሲ ጋር መወያየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በያዝነው ጥር ወር ላይ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከሚሳተፉት ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ጋር ተጨማሪ ውይይት እንደሚኖርም ነው የተናገሩት።

"በየመን የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በቀይ ባህር ላይ እየተከማቸ ያለ ሀይል አለ፤ ይሄ ሀይል እነ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ኤርትራ ያሉበት ነው፤ በዚህ ሀይል የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እና ሳኡዲ አረቢያ መኖራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ምክንያት ይህ ሀይል ለደህንነታችን አስጊ አይሆንም" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

"የሻዕቢያ መንግስትን በተመለከተ ግን እየተከታተለን የሚወስደውን እርምጃ  ምላሽ እየሰጠን እንቀጥላለን" ብለዋል። 

 

በዳዊት መስፍን

 

android_ads__.jpg