በአገራዊ ሰላምና ልማት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ "ለአገራችን ሰላምና ልማት በጋራ እንሰራለን" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ሊያካሂድ ነው።

ጉባኤው እንዳስታወቀው በሰላምና ልማት ላይ የሚመክረው መድረክ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይቆያል።

የመድረኩ ዋና ዓላማ የሃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን ሃይማኖታዊ፣ ሞራላዊና ዜግነታዊ ተልዕኳቸውን በማክበር ለጋራ ችግሮች የጋራ የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረብ ነው።

በዚህ የምክክር መድረክ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከንግድ ዘርፍ ማህበራትና ከሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች የተውጣጡ ከ400 በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መድረኩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮትን መሰረት ያደረጉ ብሄራዊ አንድነትንና ወንድማማችነትን ማጎልበት የሚያስችሉ ሃሳቦችን ይዟል ብሏል ጉባኤው።

የዜጎች እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ የጋራ መግባባት እንዲፈጠርና ተስፋ ሰጭ ልማቶች እንዲቀጥሉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም ነው ጉባኤው የጠቆመው።

በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ የሃይማኖት አባቶችና የጉባኤው ጠባቂዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ