ደስታን በመሪር ኃዘን የቀየረ ሁከት

ቅዳሜ ጠዋት። የኦሮሞ የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ዋዜማ - ቢሾፍቱ።

በርካታ ህዝብ በዓሉን ለመታደም ተገኝቷል። በዋዜማው ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች፣ ከመላ አገሪቷና ከውጪ በመጡ እንግዶች በህብረ ቀለማት ባሸበረቀ አለባበስ ወደ ስፍራው በመግባት በአካባቢውን ታድመዋል።

''የኦሮሞ ህዝብ የኢሬቻን በዓል ሲያከብር ምድሪቷ በለምለም ሳር ስላስዋብክልን፣ ከክረምቱ ከዶፍና ዝናብ በሰላም ስለአወጣኸን እናመሰግናለን” በማለት ለፈጣሪያቸው ውዳሴና ምስጋናቸውን የሚገልጹበት ልዩ በዓል ነው።

ለዚህ ነው ቢሸፍቱ በዋዜማው በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቃና አሸብርቃ የዋለችው።

በዋዜማው ከተካሄዱ ዝግጅቶች መካከል አንዱ 45ሺህ ህዝብ የተሳተፈበት የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ፣ የፈረስ ግልቢያ፣ የህጻናት ትርዒት እና የባህል ጭፈራዎች ይገኙበታል። በዚህም ከተማዋ የጎብኝዎችን ቀልብ በሚስብ መልኩ ውበትን ተጎናጽፋ ነበር።

በተለይ የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ የሁሉንም የማህብረሰብ ክፍል ያሳተፈና ለበዓሉ ድምቀት ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደ ነበር። ውድድሩ ከህጻናት እስከ አዛውንቶች አሳትፏል። በርካታ አትሌቶች የተቀመጠላቸውን የአሸናፊነት ሽልማት ለመውሰድ ተወዳድረዋል።

በዚህ የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ ከ20 በላይ ክለቦች የተውጣጡ 400 አትሌቶች እንዲካፈሉበት ተደርጓል። ይህም ከበዓሉ ድምቀት ባሻገር ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት የሚያስችል የውድድር መንፈስ ፈጥሯል። ተተኪዎች እንዲወጡ፣ አትሌቶች የግል አቋማቸውን እንዲለኩ፣ ስፖርተኞች ክለብ ለመግባት የሚያስችል ምልመላ ለማካሄድ እድል ያስገኘ ነበር።

በአገሪቷ በግላቸውም ሆነ በክለብ ታቅፈው ልምምዳቸውን የሚያደርጉ አትሌቶች በውድድር እጥርት ምክንያት ብቃታቸውን የሚፈትሹበትና የሚያሻሽሉበት እንዲሁም ሌሎቹ ታዳጊዎች ተከታዮቻቸውን በማየት በአትሌቲክሱ ስፖርት ተሳትፎ የሚነቃቁበት ሆኖ አልፍል - የስፖርት ዝግጅቱ።

ይህም ለአገሪቷ የአትሌቲክስ እድገት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ህብረተሰቡም ጤንነቱን እንዲጠብቅ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያሳትፉ ሩጫዎች እየጨመሩ ናቸው። ከጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅና በርካታ ተሳታፊዎችን በማቀፍ ውድድር ሲካሄድ መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም።

ሆኖም ቅዳሜ የተካሄደው የኢሬቻ ታላቁ ሩጫ 45 ሺ በላይ ህዝብ በውድድሩ በማሳተፍ እስካሁን ከተደረጉት የሩጫ ውድድሮች መካከል ትልቁ መሆኑን አሳይቷል።

በነጭ ቲ ሸርት የደመቀው ሩጫ ፍጹም በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መልኩ የተካሄደ ነው። ይህም የበዓሉ ድምቀት ቀድሞ ያበሰረ ነበር።
በዚሁ መድረክ ላይ አንዱ በሌላኛው ስፖርቱ በበዓል እና በፖለቲካ ላይ ሳይቀላቀሉ ነበር የተካሄዱት።

በአገሪቷ ህገ - መንግስቱ ስፖርት ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ያንጸባርቃል።

ስፖርት የኅብረተሰቡን ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ ግንኙነት የማጠናከርና ተሳትፎ የማጎልበት ድረሻው የጎላ ሚና እንዳለው በተጨባጭ የታየበት የዋዜማው ክስተት ሆኖ አልፏል።

እንደሚታወቀው በድምቀት በስፖርት ዝግጅት የተጀመረው ስነ ስርዓት መገባደጃው ላይ በሁከት እንዲገታ ሆኗል። አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል። መላውን ህዝብ ያሳዘና አገር አቀፍ የሀዘን ቀን እንዲታወጅ ያደረገም ነበር።

በርግጥ አገራችን ሃይማኖትና እምነት በነጻነት የሚከበርባት፣ ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑ ግልጽ ነው።

በዓሉን በሰላምና በደስታ ለማከበር በቦታው የተገኙ ዜጎች ሕይወታቸው በከንቱ አልፍል። በመረጋገጥና በመገፋፋት ሳቢያ ሕይወታቸውን ማጣት ያልነበረባቸው ዜጎች እንደወጡ ቀርተዋል። ለዚህ ምክንያቱ ጥቂቶች የፈጠሩት ሁከት መሆኑም በግልጽ የታየ እውነት ነው።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበል የቆየውን ታላቁን የኢሬቻ በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በሂደት ላይ ነበሩ።

በዕለቱ ከጠዋት 11 ሰዓት ጀምሮ የበዓሉን ሥነ ስርዓት ለመካፈል ወደ ከተማዋ የታደመው ህዝብ ችቦ ሙል ጨፌውን በመያዝ ወደ ባህሩ(ሆራ) በጭፈራና እልልታ ተሟል። በበዓሉ ስርዓት መሰረት መጀመሪያ ወደ ስፍራው የሚያመሩት ልጃገረዶችና ወጣቶች በመሆኑ በዚሁ መሰረት ተከናወነ።

እኛም አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች የበዓሉን ስነ-ስርዓት በምርቃትና ለመጪው ዘመን መልካም በመመኘት አስጀምረው “በድምቀት ተከብሮ ይጠናቀቃል” የሚል ሃሳብ ነበር።

የበዓሉን ደማቅ ድባብ እየተመለከትን ባህላዊ እሴቱን እያደነቅን ባለበት ወቅት ነው በድንገት ከፍተኛ ጩኸት የተሰማው። እዚህም እዛ ዋይታ የሆነው። የተቃውሞ ድምጽ ያስተጋባው። የበዓሉ መድረክ በጥቂቶች ምክንያት ወደ ሁከት ተቀየረ።

ከባህሩ ከግምት ከ300 ሜትር አካባቢ በሚገኝ መድረክ ሰብሰብ ያሉት የበዓል ታዳሚዎች በጭንቀት ውስጥ ሆነው ይታያሉ።

አባገዳዎቹ ምርቃቱን ለመጀመር መድረኩ ላይ ወጥተዋል። ብዙም አልቆዩም፤ ከታዳሚዎች መካከል ጥቂቶች የጩኸት ድምጽ አሰሙ። የሕዝብ በዓል መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ ተቃውሞ፣ ጩኸት የሚሰማበት ሆነ። ነገሮች ተደበላለቁ የመነጋገሪያ ማይኩን አንድ ታዳሚ የተከበሩ አባ ገዳዎችን ቀምቶ የተቃውሞ ድምጽ አሰማ፤ ረብሻ፣ ግርግርና ትርምስ ተፈጠረ።

የህዝቡ ደስታና እርካታ ቀርቶ ዋይታና ጩህት ተሰማ። ሕዝብ እንባ በአይኑ ሞላ፣ እሪታውና ዋይ ዋይታው ቀለጠ፤ ሰው በዱር በገደሉ መሮጥ ጀመረ። ይሸሸግበት ጥግ ፍለጋ ገባ። ገሚሱ ወደቀ፣ ተረጋገጠ። ሰዎች ቆሰሉ፤ ሞቱ። ድርጊቱ በፍጹም መከሰት አልበነረበትም፤ ግን ተከሰተ። መላውን የኢትዮጵያና የዓለም ህዝብንም አሳዘነ። አባቶች፣ እናቶችና ወጣቶች አለቀሱ። ለዘመናት ሰላምና እርቅ በሚሰበክበት፤ ሰላምና እርቅ በሚፈጠርበት፣ መልካም ምኞት በሚነገርበት ሆራ አርሰዲ ሀዘን ሰፈነ። ለሀገር ጥልቅ ሀዘን ጣለ።

የእሬቻ በዓል በዩኔስኮ ስለመመዝገቡ ሊያበስሩ በጉጉት ሲከታተሉ የነበሩት መገናኛ ብዙሃን በተቃራኒው ትርምሱንና ግርግሩን ለየመጡበት መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ። የዓይን እማኝነታቸውን ሰጡ።

ሀዘኑ የሁላችንም ቅስም ሰበረ። ደስታችን በመሪር ሃዘን ቀማን።


በዳዊት እውነቴ/ኢዜአ/