ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጳጉሜ 1 እስከ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የድርጅት የተሀድሶ ንቅናቄና ክልላዊና ሃገራዊ የህዳሴ ጉዞን አፈፃፀም በመገምገም ከሂደቱ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ትምህርቶች በመቅሰም የታዩ ድክመቶች የሚታረሙበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ኮሚቴው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የክልላችን አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በደረሰው የሰው ህይወትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡

ብአዴን ሰፊውን የአማራ ህዝብና በክልሉ የሚኖሩ ብሔረሰቦችን ታግሎ በማታገልና ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር ባካሄደው የህብረት ትግል አምባገነኑን መንግስት ካስወገደ በኋላ፣ ባለፉት 25 ዓመታት በአማራ ብሔራዊ ክልል የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት መስርቶ ክልሉን ለፈጣን እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

ብአዴን የዛሬ 25 ዓመት የአማራ ክልል የነበረበትን ሁኔታ መለስ ብሎ ሲመለከት፣ በወቅቱ የደርግ ስርዓት እንደ ስርዓት የፈረሰ ቢሆንም እንኳ፣ ለዘመናት ሲከማች ከነበረው ድህነትና ኋላቀርነት እንዲሁም ከጎጂ ልማዳዊ አስተሳሰብና ተግባራት የተነሳ፣ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ህገ-ወጥነትና ስርዓት አልበኝነት የተበራከተበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

በወቅቱ የነበረውን ስርዓት አልበኝነትና ህገ-ወጥነት በህዝብ ግንኙነት ሥራና በፀጥታ ኃይሎች ጥምረት በመቀየር፣ ለአማራ ክልል ህዝቦች የልማትና የዴሞክራሲ ምቹ ሁኔታን በመፍጠርና ሰላማዊና ህጋዊ ሁኔታን በማስፈን፣ ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በመሆን አኩሪ ተግባራትን አከናውኗል፤ ለልማትና ለዴሞክራሲ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

ድህነትና ኋላቀርነት ተከማምረው ከጠቅላላ የክልሉ ህዝብ መካከል ከግማሽ የሚልቀው ህዝብ ከድህነት ወለል በታች የነበረ ሲሆን የድህነት ምጣኔውም ከሃገር አቀፍ የድህነት መጠን በላይ ነበር፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና የአመራረት ዘይቤ፣ በዛ ላይ ደግሞ የተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ባለመዋላቸው ምክንያት፣ ዝቅተኛ ምርታማነት ፀንቶ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በመነሳት እንኳን ለአምራች ኢንዱስትሪ መስኮችና ለአገልግሎት ልማት መስፋፋት ይቅርና፣ በወቅቱ ዘጠና በመቶ የነበረውን አርሶ አደር ራሱን መግቦ ማደር አቅቶት ከባህር ማዶ የእህል እርዳታ የሚጠብቅበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

የተከበራችሁ የክልላችንና የሃገራችን ህዝቦች!

ብአዴንና የአማራ ክልል ህዝቦች፣ ባለፉት 25 ዓመታት በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ ባለፉት 13 ዓመታት፣ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም፣ ፈጣንና ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት እንዲሁም ሰፊ መሰረት ያለው የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታን ለማስኬድ ያስቻሏቸው፣ የሃገራችን ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ናቸው፡፡

ህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በከፈቱት ዕድል፣ በሃገር ደረጃ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ተነድፎ፣ መላውን የሃገራችንን ህዝቦች በእኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያሳትፍና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት ዕድል ተከፍቷል፡፡

የአማራ ህዝብና በክልሉ የሚኖሩ ብሔረሰቦች፣ ህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በከፈቱላቸው ዕድል፣ የራሳቸውን ክልላዊ መንግስት አዋቅረው ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ዕድል ተጎናጽፈዋል፡፡ የክልሉ ህዝቦች ያላቸውን የጉልበት፣ የመሬት፣ የካፒታልና የእውቀት አቅም አሰባስበው የመልማትንና ነፃ የምርት ተጠቃሚነትን ዕድል ተጎናጽፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ህዝቦች ከክልላዊ ልማት፣ ከዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና ከተጠቃሚነት ባሻገር፣ በሃገር ደረጃ በተመጣጣኝ ውክልና ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል ሁኔታም ተመቻችቶላቸዋል፡፡

በመሆኑም ሰፊው የአማራ ህዝብም ሆነ በክልሉ የሚኖሩ ብሔረሰቦች፣ ሰላማቸውን በቀጣይነት እያጠናከሩ ከመሄዳቸውም በላይ፣ የተከተሉት ግብርና መር የልማት አቅጣጫ ምርታማነታቸው ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ ተነስቶ ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡

ከዚህ በመነሳት የክልሉ የሰብል ልማት፣ ክልሉን በምግብ ሰብል ራሱን ያስቻለ ከመሆኑም በላይ፣ በአገር አቀፍ ደረጃም አወንታዊ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በተፈጥሮ ሀብትና በአካባቢ ጥበቃ ማነቃነቅ በመቻሉ፣ ለዘመናት ተራቁተው የቆዩ ተራሮች ወደ ነባር ይዞታቸው እንዲመለሱ፣ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ እንዲሻሻልና በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረው ግብርና በአማራጭ የመስኖ ልማት እንዲስፋፋና ግብርናችን ወደ ክረምት ከበጋ የልማትና የምርት እድገት ውስጥ እንዲገባ ብአዴንና አርሶ አደሩ የተቀናጀ ጥረት አካሂደዋል፡፡

ከሰብል ልማት በተጓዳኝ፣ የደን ልማትና የእንስሳት ሀብት ልማት ምርታማነት እንዲሻሻልም ብዙ ተግባራት የተከናወኑ ከመሆኑም በላይ፣ ለቀጣይ የዘርፉ ልማት ያከማቸናቸው ምርጥ ተሞክሮዎችና አቅሞችም በርካታዎች ናቸው፡፡ ገጠሩን ለማልማት በተካሄደው ጥረት የአርሶ አደሩ ገቢ እንዲሻሻል አስችሏል፡፡

ሀብት የፈጠሩ የአርሶ አደሮች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡ድህነትም ከነበረበት ደረጃ ከግማሽ በታች ወርዷል፡፡ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የውጭ እርዳታን የምንጠብቅበት ታሪክ ተቀይሮ፣ በመንግስትና በህዝብ የጋራ ጥረት የምንቋቋምበትን አቅም እንደገነባን የ2008 ዓ.ም አፈፃፀማችን ጉልህ ማሳያ ነው፡፡

የብአዴን አመራር፣ በግብርና ልማት ሳይታጠር፣ በከተሞች ልማትን ለማስፋፋት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን አካሂዷል፡፡ የከተሞች ልማት ከሃገር አቀፉ አማካኝ በታች እንደነበርም ይታወቃል፡፡ በከተሞች የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና ተጓዳኝ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ ከተሞቻችን የአምራች ኢንዱስትሪዎችና የንግድ አገልግሎት ማዕከላት እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል፡፡

በከተሞች ተንሰራፍቶ የቆየው ህገ-ወጥነትና የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ የተደፈቀ ባይሆንም፣ በተነፃፃሪ የልማታዊነትና የዴሞክራሲያዊነት አስተሳሰብና ተግባር እንዲስፋፋ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ተካሂደዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪ መስኮችን ለማስፋፋት የጥቃቅንና አነስተኛ ተዋናዮችን በማደራጀት፣ የስልጠና፣ የብድር፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶች፣ በመስኩ የተሰማሩትን ወገኖች ተጠቃሚ ከማድረጋቸውም በላይ ለቀጣይ አቅም የሚሆኑ ውጤቶችም ተገኝተውባቸዋል፡፡

ከአርሶ አደሩና ከግብርና ልማታችን ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለው አቅም፣ ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት የጥሬ እቃ እና የገንዘብ ምንጭ ሆኖ፣ ለቀጣይ ልማታችን አቅም በሚፈጥርበት ሁኔታ እየተገነባ በመምጣቱ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማቱ ተጀማምሯል፡፡

ብአዴንና ህዝቡ ባካሄዱት የጋራ ጥረት በማህበራዊ ልማት መስክም ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ከዓመታት በፊት ከአገር አቀፍ አማካኝ የትምህርት ተሳትፎ በታች የነበረው የትምህርት ተደራሽነት ታሪክ ተቀይሮ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ህፃናትና ታዳጊዎች በትምህርት ገበታ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ይህ ከክልሉ ነዋሪ አንድ አራተኛ የሚሆነውን የሚሸፍን ከመሆኑም በላይ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በተካሄደው ጥረት በየትምህርት እርከኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማበራከትም ተችሏል፡፡

በጤና ልማት መስክ፣ መከላከልን ማዕከል ባደረገ የጤና ልማት ንቅናቄ ወባና መሰል ተላላፊ በሽታዎችን መግታት ከመቻሉም በላይ፣ ከመከላከል አልፎ የሚመጣን በሽታ አክሞ ለመፈወስ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት ተችሏል፡፡

በመስኩ የሰው ኃይል ልማትና የህክምና መርጃ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የህክምና አገልግሎቱን ለማሻሻል ያስቻሉ ተግባራትም ተከናውነዋል፡፡ ይህም ጤናማና አምራች ህብረተሰብ ለመገንባት እያስቻለ ይገኛል፡፡

በብአዴን የሚመራው የክልሉ መንግስት፣ ከህዝቡ ጋር በመሆን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶችን ከማስፋፋት ባሻገር፣ ከከተማ እስከ ገጠር የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማስፋፋትና ጥራታቸውንም ለማሻሻል ጥረቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡

ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ባሻገርም የመልካም አስተዳደር እና መሰረተ ሰፊ የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባራት በመከናወን ላይ ሲሆኑ፤ ለውጥም በማምጣት ላይ ናቸው፡፡

የተከበራችሁ የክልላችንና የሃገራችን ህዝቦች!

የተመዘገቡት ውጤቶች ለቀጣይ ልማትና ሁለንተናዊ ለውጥ አቅም የሚሆኑ ሁኔታዎች የፈጠሩ ቢሆንም፤ በየጊዜው እየተደማመሩ የመጡ፣ በወቅቱ ያልተፈቱ መሰረታዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንዲሁም፣ ወቅታዊ ጉዳዮች ተበራክተው፣ በየጊዜው ታዳጊ ፍላጎቶቹን እያነሳ ያለውን ህዝባችንን ወደ ቅሬታ፣ አለመግባባትና ግጭት ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ተፈጥሮ በህይወትና በንብረት ላይ የሚያሳዝን ጉዳት ደርሷል፡፡

ከመሰረታዊና ወቅታዊ ችግሮች መካከል፣ በጥሩ አቅጣጫ የተጀመረው የግብርናም ሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት መስኮች ምርታማነት በሚፈለገውና መሆን በሚገባው ደረጃ እንዳልሆነና አሁንም ይበልጥ ጠንክረን መስራት እንዳለብን ግልጽ ሆኗል፡፡

ከምርት አቅርቦት አለመስፋፋት እንዲሁም፣ ከመሸመት አቅም አለማደግ ጋር የተያያዘ የኑሮ ውድነት፣ በገጠርም ሆነ በከተሞች እየተበራከተ የመጣው ስራ አጥነት፣ ከአገልግሎት አሰጣጥና የልማት ችግሮችን ካለመፍታት ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በጉልህ ተስተውለዋል፡፡

አሁንም ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚመጣን የድርቅ አደጋና እሱን ተከትሎ የሚከሰተውን የረሃብ አደጋ መቋቋም የሚችል የግብርና ልማት፣ በቤተሰብና በአካባቢ ደረጃ በአግባቡ አልገነባንም፡፡ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም ጥቂት አይደሉም፡፡

ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝባችን ከነበረው ከግማሽ በላይ የቀነሰ ቢሆንም፣ ድህነት አሁንም ከክልላችን ሊወገድ የሚገባ ከባድ ችግር እንደሆነ ይገኛል፡፡

ከመሰረታዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች ባሻገር፣ ከወሰን እና ከማንነት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ማዕከል በማድረግ፣ በወቅቱና በአግባቡ ምላሽ ካለመሰጠቱ የተነሳ፣ አለመግባባቶችና ቅሬታዎች እየተባባሱ ሄደው በድርጅታችንና በህዝባችን መካከል ቅሬታዎች፣ አለመግባባቶችና ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በዜጎቻችንና በፀጥታ አስከባሪ ኃይሎቻችን ላይ የሚያሳዝን ጉዳት ደርሷል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የተዘረዘሩት መሰረታዊና ወቅታዊ ችግሮች መንስኤዎች ምንድን ናቸው? የሚሉትን ጉዳዮች በጥልቀት ገምግሞ ለይቷል፡፡ የችግሮቹ ዋነኛዎቹ መንስኤዎች፣ በትግሉ ሂደት የመንግስትን ስልጣን የህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ በማድረግ መንቀሳቀስ እየቀነሰ፣ አመራርነት የኑሮና የጥቅም መሰረት የመሆን ዝንባሌ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር የተያያዙ ችግሮች መሆናቸውን አስምሮበታል፡፡

በድርጅት ውስጥ ለስልጣን ያለው የተዛባ አተያይ፣ በመርህ ላይ ቆሞ የመታገል ሂደቱን በማዳከሙ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮች እየተባባሱ እንዲሄዱ አድርገዋል፡፡

የአመራር መሰረታዊና የዘወትር ተልዕኮው የህዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበር ያላሰለሰ ትግል ማካሄድ ሲገባ ከተሳሳተ ዝንባሌ የተነሳ በጅምር ላይ ያለው የለውጥ ጉዞ ችግሮች እየተጫጫኑት የህዝብ ቅሬታ ሊባባስ ችሏል፡፡ ይህን ተከትሎ በተለይ የወጣቶቻችን ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድ አለመቻሉም ለወጣቶች ቅሬታ መባባስ ምክንያት እስከ መሆን ደርሷል፡፡

በተጠቀሱት ችግሮች የተነሳ በአንድ ወቅት ተዳክሞ የነበረው የትምክህት አስተሳሰብና ተግባር ቀስ በቀስ እየሰረገ ሂዶ፣ የአመራሩንና የአባላትን አስተሳሰብ አዛብቷል፤ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ቀላል ባልሆነ ደረጃ በመስፋፋቱም ለዓመታት በአብሮነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እየገነባ በመጣው ህብረተሰባችን ውስጥ ህዝባዊና አገራዊ አንድነትን የሚያዳክሙ የተሳሳቱ ተግባራት ተከስተዋል፡፡

ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብና ተግባር የሰፊውን የአማራ ህዝብ የማይወክል ተግባር ከመሆኑም በላይ ድርጅታችንንና ህዝባችንን ያሳዘነ ሆኗል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችንና የሃገራችን ህዝቦች!

በድርጅታችን አመራር ያጋጠሙትን ችግሮች መነሻ በማድረግ፣ ህዝባችን ውስጥ የተከሰተውን ቅሬታና አለመግባባት እንደመልካም አጋጣሚ ቆጥረው ህገ-መንግስቱንና ስርዓቱን ለማፍረስ የተነሱ የአመጽ ኃይሎች፣ የአማራን ህዝብ ከአገራችን ህዝቦች ለመነጠል የጥፋት ተግባራቸውን አቀነባብረው ሲፈጽሙ ታይተዋል፡፡

የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ ወደ ግርግርና አመጽ መውሰድ የፈለጉ ኃይሎች፣ ችግሮችን አሳድገውና አዛብተው አውዳሚና ደም አፋሳሽ ቅስቀሳዎችንና የአመጽ ተግባራትን በማቀነባበር ለዘመናት በአብሮነት የኖሩትን ህዝቦቻችንን በጥርጣሬና በጥላቻ አይን እንዲተያዩ በማያቋርጥ ሁኔታ ሰርተዋል፡፡

የሃገራችን ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ፣ ለሁሉም እኩል እድል የፈጠሩ ሆነው ሳለ፣ በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት የሚገለፁ ጥፋቶችን የፈፀሙ ሙሰኞች ከየትኛውም ብሔር ይምጡ፣ በህገ-ወጥ ተግባራቸው ሊጠየቁ ሲገባ፣ ይህንን ሰበብና መነሻ በማድረግ ብሔራዊ አድሎ እንዳለ አድርገው ህዝብን ከህዝብ የሚያፋጅ ተግባር በተቀነባበረ አግባብ ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ይህ ተግባራቸው እነዚህ የአመጽ ኃይሎች፣ ህዝብን ከህዝብ ከማፋጀት ወደ ኋላ እንደማይሉ በቅርቡ በተከሰቱ አብነቶች ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ይህን የጥፋት ተግባር ህዝቡ በንቃት ተገንዝቦ ሊመክተው ይገባል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችንና የሃገራችን ህዝቦች!

ችግሮች ባጋጠሙት ቁጥር በህዝባዊ ወገንተኝነትና በዓላማ ጽናት መንፈስ ፈተናዎችንና ተግዳሮቶችን የማለፍ ተሞክሮና ብቃት ያለው ብአዴን፤ በኢህአዴግ ደረጃ የተጀመረውን አገር አቀፍ የመሰረታዊ ለውጥ ንቅናቄ መነሻ በማድረግ በጥልቀት የመታደስ አስተሳሰብን ይዞ ከፍተኛ ንቅናቄ ለማካሄድ ተነሳስቷል፡፡

ብአዴን እየተደማመሩ የመጡ መሰረታዊና ወቅታዊ ችግሮች፣ እንዲሁም ፈተናዎች፤ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን እየተፈታተኑ እንደሆነ ገምግሟል፡፡ ችግሮችን በጥልቀት ፈትሾ ድክመቶችን ከህዝቡ ጋር በመሆን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታትም ተዘጋጅቷል፡፡

በመሆኑም ብአዴን ለመላው የአገራችንና የክልላችን ህዝቦች እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ እያለ የጀመርነውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ ከግቡ ለማድረስ ሁሉም ህዝቦች እንዲሳተፉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የብአዴን አባላትና የትግሉ ደጋፊዎች!

ብአዴን በአባላቱና በደጋፊዎቹ ግንባር ቀደም ተሳትፎ፣ ባለፉት ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ መስኮች ሁሉ የህዝባችንን ህይወት ያሻሻሉና የክልላችንና የአገራችን እድገት ወደፊት የሚያራመዱ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ዛሬም ያጋጠሙ መሰረታዊና ወቅታዊ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን ለመፍታት ተዘጋጅቷል፡፡ ብአዴን እንደወትሮው ሁሉ በህዝባዊነትና በጽናት ትግሉን ሊቀጥልበት ተዘጋጅቷል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ የለኮሰውን ንቅናቄ በማቀጣጠል ለተሟላ የለውጥ ሂደት በግንባር ቀደምነት እንድትሰለፉ ብአዴን ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የእህትና የአጋር ድርጅቶች አመራሮችና አባላት

በኢህአዴግ ደረጃና በየብሔራዊ ድርጅቶቻችን ባረጋገጥነው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አመራር፣ ትልልቅ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ውጤቶችን አስመዝግበናል፡፡ የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ያጋጠሙንን መሰረታዊና ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታትም በግንባራችን መሪነት በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን ጀምረናል፡፡

ብአዴን በአማራ ክልል ሁኔታም ሆነ በአገር ደረጃ ንቅናቄውን ለማፋጠን ዝግጁነቱን እየገለፀ፣ በጀመርነው የለውጥ ጎዳና ተጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአማራ ክልል አርሶ አደሮች !

በብአዴን መሪነትና በእናንተ በክልላችን አርሶ አደሮች ሙሉ ተሳትፎ፣ ግብርናን ማዕከል ባደረገው ልማታችን በሁሉም የህይወት መስኮች ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሆነ ከእናንተ በላይ ምስክር አያሻም፡፡

የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲመጣ እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከልማትና ከፍትሀዊ አገልግሎት ተደራሽነት ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች በአስተማማኝ ደረጃ እንዲፈቱ፣ ብአዴን የለውጥ ንቅናቄን ሰንቆ ቀርቧል፡፡

በመሆኑም ችግሮቹን ነቅሳችሁ፣ የመፍትሄ ሀሳብ በማቅረብና በተግባራዊ ለወጡም እንደካሁን ቀደሙ ሁሉ ንቁ ተሳትፎ እንድታደርጉ ብአዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ከተማ ነዋሪዎች ምሁራንና ባለሀብቶች!

የክልላችን ከተሞች የአምራች ኢንዱስትሪና የንግድ ማዕከል በሚሆኑበት ደረጃ፣ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን ስናካሂድ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ከተሞች ለዘመናት ተንሰራፍቶ ከቆየባቸው የኪራይ ሰብሳቢነትና የህገ-ወጥነት ነባራዊ ሁኔታ ተላቀው፣ በምትኩ ልማታዊና ህጋዊ ሁኔታ የሰፈነባቸው እንዲሆኑ፣ ለከተማው ንዑስ አምራችም ሆነ ለባለሀብቱ ልማታዊ ጥረት እንዲመቹ የተሰሩ ስራዎች አሉ፡፡

ይሁንና አሁንም ህገ-ወጥነትና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች፣ መሰረታዊ ለውጥ የሚሹ እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ችግሮቹን በመፍታት ከተሞቻችንን ለልማትና ለፍትሀዊ አገልግሎት የተመቹ ለማድረግ ብአዴን ተዘጋጅቷል፡፡ በመሆኑም ከንቅናቄው ጎን ተሰልፋችሁ የድርሻችሁን እንድታበረክቱ ብአዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የሃገር መከላከያና የፀጥታ ኃይሎች!

በክልላችንም ሆነ በአገራችን እየተገነባ ያለው ሰላማዊ ሁኔታ ተጠናክሮ፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ የተመቸ እንዲሆን፣ ህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የሰጣችሁን ህዝባዊ አደራ በመወጣት ረገድ ድርሻችሁ ከፍተኛ እንደነበር ብአዴን ያምናል፡፡

በቅርቡ በአማራ ክልል የተከሰተውን ችግር በመቀልበስ ህግንና ስርዓትን ለማስፈን፣ የህዝባችን ደህንነት፣ ሀብትና ንብረት ከጥፋት ለመታደግ ያደረጋችሁትን ጥረትም በአድናቆት ይመለከታል፡፡

አሁንም ሰላማዊነትና ህጋዊነት ተጠናክረው፣ ለዜጎች ህይወት የተመቸ ሁኔታ እንዲፈጠር የምታደርጉትን ጥረት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ብአዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ሴቶች!

በገጠርም ሆነ በከተሞች በሁሉም መስኮች፣ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብአዴን አመራር እየሰጠ መጥቷል፡፡ የተመዘገቡ ለውጦች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ የሴቶችንም ሆነ የጠቅላላ ህብረተሰቡን ለውጥ ከማፋጠን አኳያ መሰረታዊና ወቅታዊ ችግሮች እንዳጋጠሙትና ችግሮቹ በመሰረታዊነት መፈታት እንዳለባቸው ብአዴን ወስኗል፡፡

በመሆኑም የለየናቸው ችግሮች በአስተማማኝ ደረጃ እንዲፈቱና የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ብአዴን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ወጣቶች!

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሰላምን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን እንዲሁም የዴሞክራሲ ግንባታን በቀጣይነት የማረጋገጥ ተግባራት፣ የወጣቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደመጡ አያከራክርም፡፡

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የወጣቱን የኢኮኖሚ ችግሮች ከመፈታት ጋር የተያያዙ የተሳታፊነትና የተጠቃሚነት ጉዳዮች ጥያቄ እየተነሳባቸው መቆየታቸውን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም የስራ አጥነት ችግር እየተስፋፋ መምጣቱን ብአዴን በጥልቀት ገምግሟል፡፡

የስራ አጥነትና ተጓዳኝ ችግሮች በራሱ በወጣቱ ተሳትፎ፣ በህብረተሰቡና በመንግስት ጣምራ ጥረት ሊፈቱ እንደሚችሉም ብአዴን ያምናል፡፡ የወጣቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ፍላጎቶች እውን የሚሆኑበት ሰላምና የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡

በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ ዝግጅት በማካሄድ ላይ ነው፡፡ በሚካሄደው ጥረት ከብአዴን ጎን እንድትሰለፉ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

 

 

 

 

 

 


በጥልቀት በመታደስ ክልላዊና አገራዊ ህዳሴያችንን እናፋጥናለን!!

ዘለዓለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!!