ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እይታ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 21፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው ሳምንት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ካገኘችባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል መንገድ አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በመንገድ የማስተሳሰሩ ሂደት በክፍለ አህጉሩ የጋራ የምጣኔ ኃብት እድገት እንዲሳካ ያደርጋል ብላ እንደምታምን ወርልድ ቡለቲን ድረ-ገጽ አስነብቧል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙን ጠቅሶ ዘገባውን ያቀረበው ድረ ገጹ የሚገነቡት መንገዶች ኢትዮጵያን ከሱዳን፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ያገናኛሉ ብሏል።

ይህም በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሷል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ የወደብ አቅርቦት በስፋት እንድታገኝ ከማስቻሉም በላይ አገሪቱ የግብርና ውጤቶቿን ለውጭ ገበያ እንድታቀርብ፤ ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን ደግሞ ወደ አገር ውስጥ እንድታስገባ ያግዛታል ብሏል፡፡

ከአሶሳና ከሽሬ ተነስተው እስከ ሱዳን ድረስ የሚዘረጉት መንገዶችም ይህን ዓላማ እውን እንደሚያደርጉ ነው የገለጸው፡፡

ግንባታቸውን የተጠናቀቀው ከጋምቤላና ሚዛን ተፈሪ ተነስተው ደቡብ ሱዳን የሚያደርሱ ሁለት የአስፓልት መንገዶችና በግንባታ ላይ ያለው ከአዲስ አበባ ኬንያ የሚዘረጋው መንገድ ኢትዮጵያን ከአጎራባች አገራት ጋር ከማገናኘት ባለፈ የውጭ ኢንቨስትመንትን ይስባሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

በሌላ ዜና ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን በማስተናገድ እየፈፀመች ያለችው በጎ ተግባር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊታገዝ ይገባል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድረ-ገጹ አስነብቧል፡፡

በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን የእርስ በእርስ ግጭት ተከትሎ በየወሩ 25ሺህ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፤ ከስደተኞቹም የ90 በመቶውን ድርሻ ሴቶችና ህጻናት ይይዛሉ፡፡

ምንም እንኳን የኢኮኖሚ አቅማቸው ከባለጸጎች ጎራ ባይመደብም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ስደተኞችን ለመቀበል በራቸውን ክፍት ማድረጋቸው ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ተምሳሌት ነው ብሏል፡፡

እስካሁን ድረስ ከ193ቱ የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት መካከል ስደተኞችን በመርዳት 18ቱ ብቻ ናቸው እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት። ሌሎችም በተለይም የኢትዮጵያን ፈለግ መከተል እንዳለባቸው ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

ምክንያቱም የስደተኞቹን የምግብ፣ የጤና አገልግሎት፣ የመጠለያና የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት ድርጅቱ ያስፈልጋል ብሎ ከተገመተው 211 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 25 በመቶው ብቻ ነው የተገኘው፡፡

ስለዚህ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን የሚቀበሉ አገራትን ለማገዝና ቀሪውን ገንዘብ ለማሟላት እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የተከሰተው አሳዛኝ ቀውስ በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ መረባረብ እንደሚኖርበት ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዋና ፀኃፊ ታሊብ ሪፋይ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የድርጅቱ ድረ-ገፅ ኢትዮጵያ የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ የሚታደርገውን ጥረት አሞግሷል፡፡

አገሪቱ የቱሪስት መስህቦቿን ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ የሰጠችው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነና ለእድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ዋና ጸኃፊው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በመሰረተው የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በኩል ዘርፉን ለማሳደግ የመንገድ ግንባታ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ የአቅም ግንባታ ስራን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የምክር ቤቱ ስራ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ እሴቶች በቱሪዝም ዘርፍ በማስተዋወቅ አገሪቱን ከአፍሪካ ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች አንዷ ማድረግና ዘርፉን በአገሪቱ የእድገት ሂደት ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ማድረግ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእምቅ ታሪካዊ ሃብቶች ባለቤት ናት፤ ሀብቶቿም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኙ መንግስት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማሰማራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ማለታቸውን ድረ-ገጹ አስነብቧል፡፡

በቀጣይም ዘርፉን ለማሳደግ በሚረዱ እንቅስቃሴዎች ላይ በጋራ ለመስራት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የተባበሩት መንግስታት የአለም የቱሪዝም ድርጅት ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጎን ለጎን የአገሪቱን የዱር እንስሳት መንከባከብና ማስተዋወቅ ላይ ተሰማርቷል ሲል ያስነበውን ደግሞ የቶምሰን ሮይተርስ ፋውንዴሽን ድረ-ገፅ ነው፡፡

የአገሪቱ የዱር እንስሳት ኃብት ከቱሪስት መስህብነት በተጨማሪ የታሪክ አካል መሆኑን የገለጸው ድረ-ገጹ ለጥበቃ እንዲያመችም የዱር እንስሳቱንና አካባቢያቸውን የሚጠብቅ ተቋም በብሔራዊ ደረጃ መቋቋሙን አመልክቷል።

ተቋሙ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በሚያደርሱትን የደን መመንጠርና የአፈር መሸርሸር አደጋ ለመከላከል እንደሚሰራም ነው የጠቆመው።

በሰዎች በሚደርሱ ጥፋቶች በብዛት የተጎዱ አከባቢዎችን ማስተካከልና ነዋሪዎች የተፈጥሮ ኃብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግ የተቋሙ ዋና አላማ መሆኑም ነው በድረ-ገጹ የተመለከተው፡፡