በፕሪምየር ሊጉ ለዋንጫ የሚፎካከሩት ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ጥለዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው እለት በክልል ከተሞች ስታዲየሞች ቀጥለው ተካሂደዋል።

ዛሬ በትግራይ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ መቐለ ከተማ በሜዳው ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማስተናገድ ድል ቀንቶታል።

መቐለ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ0 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን፥ የመቐለ ከተማን የማሸነፊያ ጎል ጋቶች ፓኖም በ90ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ጎንደር ፋሲለደስ ስታዲየም ላይ በተደረገ ጨዋታም ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና የተገናኙ ሲሆን፥ ፋሲል ከነማ ጨዋታውን 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የፋሲል ከነማን የማሸነፊያ ጎልም ሀሚዝ ጊዛ በ7ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

ድሬ ደዋ ላይ ደግሞ ድሬ ደዋ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ የተገናኙ ሲሆን፥ ጨዋታውም 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ነው የተጠናቀቀው።

በጨዋታው ላይም እንዳለ ከበደ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል አርባ ምንጭን መሪ አድርጋ የነበረ ቢሆንም፤ በረከት ይስሀቅ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ለድሬ ደዋ ያስቆጠራት ጎል ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

በሀዋሳ ስታዲየም የተካሄደው የሀዋሳ ከተማ እና የወልዋሎ አዲግራት ጨዋታም ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ የተደረገው የአዳማ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታም ያለምንም ግብ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በተመሳሳይ በሶዶ ስታዲየም የተደረገው የወላይታ ድቻ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታም 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል።

የጅማ አባጅፋር እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ መጣልም የፕሪምየርሊጉን ዋንጫ ማን ያነሳል የሚለው አሁንም እንዲጠበቅ አድርጓል።

ፕሪየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር በእኩል 52 ነጥብ እና 19 ጎል 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

መቐለ ከተማ በ49 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ዛሬ ነጥብ የጣለው የኢትዮጵያ ቡና በ47 ነጥብ ወደ 4ኛ ደረጃ ተንሸራቷል፤ አዳማ ከተማ በ44 ነጥብ በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።