አሜሪካ፣ ካናዳና ሜክሲኮ የ2026 ዓለም ዋንጫን በጋራ እንዲያዘጋጁ ተመረጡ

አዲስአበባ፣ ሰኔ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ2026 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ወደ ሰሜን አሜሪካ ያቀና ሲሆን አሜሪካ ፣ ካናዳና ሜክሲኮ ናቸው ውድድሩን በጋራ የሚያስተናግዱት ተብሏል፡፡

የ2026 የዓለም ዋንጫ ሦስት ሀገራ በአንድ ጊዜ ሲያስተናግዱት የአሁኑ የመጀመሪያ ነው ተብሎለታል፡፡

ከ203 ጠቅላላ መራጮች ውስጥ ሰሜን አሜሪካኖቹ 134 ድምጽ ሲያገኙ ሞሮኮ 65 ድምጽ በማግኘት ተሸንፋለች፡፡

ምርጫው የተካሄደው የ2018 የዓለም ዋንጫን በምታስተናግደው ሩሲያ ሞስኮ ውስጥ ነው፡፡

በ2026 የዓለም ዋንጫ 80 ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን አብዛኛው ጨዋታ በአሜሪካ ምድር ይካሄዳል፡፡

10ሩ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በካናዳ፣ 10ሩ በሜክሲኮ እና የፍጻሜ ውድድሩን ጨምሮ 60 ጨዋታዎች ደግሞ በአሜሪካ አዘጋጅነት ለማሰናዳት መዘጋጀታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሜክሲኮ በታሪኳ በ1970 እና በ1980 ሁለት የዓለም ዋንጨዎችን ስታስተናግድ አሜሪካ ደግሞ በ1994 አንድ ጊዜ አስተናግዳለች፡፡

በአንጻሩ ካናዳ የዓለም ዋንጫን የማስተናገድ ዕድል ስታገኝ ይህ የመጀመሪያዋ ነው፡፡

ውድድሩን ለማዘጋጀት አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ሰፊ የማሸነፍ ግምት ቢሰጣትም ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች አንጻር በመሰረተ ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ሊሳካላት አልቻለም፡፡

ሦስቱ የሰሜን አሜሪካ ሀገራት 23 ያለቁ የተዘጋጁ ስታዲየሞች ሲኖሩዋቸው ሞሮኮ በአንጻሩ ማስፋፊያ የሚያስፈልጋቸውና አዳዲስ ስታዲየሞች ያስፈልጓት ነበር ተብሏል፡፡

ሦስቱ ሀገራት በ2026 የዓለም ዋንጫ ውድድር 11 በሊለየን ዶላር ትርፍ ለማስገባት ለዓለም አቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሺን ቃል መግባታቸው ተገልጿል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ዋንጫ ቡድኖች ከ32 ተወዳዳሪዎች ወደ 48 ያድጋሉ ተብሏል፡፡

 

 

 

 

ምንጭ፦ኒውዮርክ ታይምስ
በአብርሃም ፈቀደ ወደ አማርኛ ተመለሰ