የወለዋሎና የመቐለ ጨዋታ ዛሬ የማይካሄድ ሲሆን፥ ሌሎች ተስተካካይ ጨዋታዎች ይከናወናሉ

አዲስ አባባ፣ ግንቦት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ የሚጀመር ሲሆን፥ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲና የመቐለ ከተማ ጨዋታ የክልሉ ኮማንድ ፖስት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ዛሬ አይካሄድም ተብሏል፡፡

ወልዋሎና መቐለ ዛሬ እንዲጫወቱ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበረ ቢሆንም፥ ጨዋታው ዛሬ እንደማይካሄድ የትግራይ ክልል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ይጫወታሉ መባሉም ስህተት ነበር ብሏል፡፡

ዛሬ በሚካሄዱ ሌሎች ተስተካካይ ጨዋታዎች አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ወላይታ ድቻን በ9፡00 ሰዓት ይገጥማል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮኤሌክትሪክና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 9፡00 ሰዓት ይገናኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ለሶስት ሳምንታት ማንኛውንም ውድድር እንደማይዳኙ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ተቋርጠው እንደቆዩ የሚታወስ ነው።

ፌዴሬሽኑና የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር ፕሪምየር ሊጉ እንዲቀጥል መስማማታቸውን ተከትሎ ፕሪምየር ሊጉ ረቡዕ ግንቦት 15 በሚካሄዱ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎችም ቀጥ ይውላ፡፡

በዚህም መሠረት ረቡዕ ግንቦት 15 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ በአዲስ አበባ ስታድየም 8:00 ላይ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከመከላከያ ድሬደዋ ላይ፣ ሀዋሳ ከተማ ከፋሲል ከተማ ሀዋሳ ላይ፣ አዳማ ከተማ ከመቐለ ከተማ አዳማ ላይ፣ ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ወላይታ ሶዶ ላይ፣ ወልዲያ ከኢትዮጵያ ቡና ሰበታ ላይ፣ ጅማ አባጅፋር ከአርባምንጭ ከተማ ጅማ ላይ በተመሳሳይ በ9:00 እንዲሁም ደደቢት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲስ አበባ ላይ በ10:00 በሚያደርጉት ጨዋታ የሊጉ ውድድር እንደሚጀምር ታውቋል።

ጅማ አባ ጅፋር ፕሪምየር ሊጉን በ39 ነጥብ ሲመራ፥ መቐለ ከተማ በ35 ነጥብ እንዲሁም ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ33 ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ።