የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተመሰረተበት 75ኛ ዓመት ማጠቃለያ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው የ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የማጠቃለያ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሄደ።

"ባንኬ ኩራቴ" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ 13 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ በወንዶች የሐዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ተወዳዳሪው ጥላሁን ኃይሌ 21 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል።

በሴቶች ደግሞ የአሰላ ስፖርት ክለብ ተወዳዳሪዋ አትሌት ፀሐይ ገመቹ 24 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ አሸንፋለች።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ለወጡ አትሌቶች የ75፣ የ40 እና የ20 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ዳግም ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የሩጫ ውድድሩ ባንኩ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት ማክበርና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ዋነኛ ዓላማ ነው።

የባንኩን 75ኛ ዓመት ምስረታ በማስመልከት በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም በሃዋሳ፣ መቐለና ባህርዳር የ7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል።

ከሶስት ሳምንት በኋላ የትራፊክ ደህንነት ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማው ያደረገ የ6 ኪሎ ሜትር የዱላ ቅብብል ሩጫ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

የሃገር ገጽታን ማስተዋወቅ፣ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትና የህብረተሰቡን የስፖርት እንቅስቃሴ ባህል ማሳደግ፥ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ዋነኛ ግብ አድርጎ የሚሰራባቸው ጉዳዮች እንደሆኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ75ኛ ዓመት አከባበር የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው ውድድሩ የባንኩን የ75 ዓመታት የስኬት ጉዞ ለማሰብ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የባንኩ ደንበኞች፣ ሰራተኞች፣ አመራሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተወዳደሩበት ይህ ውድድር ከክብረ በዓሉ ባለፈ በማህበረሰቡ መካከል፣ የእርስ በእርስ ትውውቅና ትስስር በመፍጠር ረገድ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ እንደነበርም ገልጸዋል።