ሉሲዎቹ የሴካፋ ውድድር ላይ ለመካፈል ሐሙስ ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ

አዲስ አባባ፣ ግንቦት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን፤ ሉሲዎቹ የሴካፋ ውድድር ላይ ለመካፈል ሐሙስ ወደ ሩዋንዳ ያቀናሉ፡፡

በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄደው ውድድር ከግንቦት 10 እስከ ግንቦት 20 ቀን ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በዚህ ሳምንት ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም የሩዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ ከሴካፋ ባለማግኘቱ ውድድሩን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሞ እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም ሴካፋ ሩዋንዳ የጠየቀችውን ገንዘብ ገቢ እንደሚያደርግ ማሳወቁን ተከትሎ ውድድሩ በድጋሚ ግንቦት 10 ላይ እንደሚጀመር ይፋ ሆኗል፡፡

የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የተለያዩ የአፍሪካ የብሔራዊ ቡድንና የክለቦች ውድድር ለማስተናገድ የፋይናንስ ችግር በስፋት ሲገጥመው ይስተዋላል።

ከሁለት ዓመት በፊት ኡጋንዳ ውድድሩን ካስተናገደች በኃላ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በበጀት ማጣት ምክንያት መዘግየቱ ይታወሳል።