38ኛው የሸገር ደርቢ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 15 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ዛሬ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።

በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ በሚደረገው የዋንጫ ፉክክር እድሉ ያላቸው ሁለቱ አንጋፋ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊ ሆኗል።

የድል ጎሏን ሙሉዓለም ጥላሁን በ88ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ድሉን ተከትሎም በአህጉራዊ ውድድር ምክንያት ሶስት ቀሪ ጨዋታዎችን ያላደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ጅማ አባ ጅፋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በሶስት ማጥበብ ችሏል።

ፈረሰኞቹ አሁን በሊጉ በ33 ነጠብ በግብ ክፍያ ተበልጠው ወደ ሶስተኛ ደረጃ መምጣት ችለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በያዘው 32 ነጥብ ወደ 5ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል።

 ሁለቱ ክለቦች እስከዛሬ ባደረጉት የእርስ በርስ ጨዋታ የዛሬውን ጨምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 17 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ፥ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 6 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል።

14 የእርስ በርስ ግንኙነቶች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፤ ሊጉን ጅማ አባ ጅፋር ከ21 ጨዋታዎች በሰበሰበው 38 ነጥብ ሲመራ ደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ በእኩል በ33 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


ተጨማሪ መረጃ ከሶከር ኢትዮጵያ