በፕሪምየር ሊጉ ደደቢት ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር መሪነቱን ይዟል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው እለት በአዲስ አበባና በክልል ከተማ ስታዲየሞች ቀጥለው ተካሂደዋል።

ዛሬ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደ ጨዋታ መቐለ ከተማ ከወልዲያ 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ወደ ጎንደር ያመራው መሪው ደደቢት በፋሲል ከነማ 1 ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በጨዋታው ላይ ፊሊፕ ዳውዝ የፋሲል ከነማን የማሸነፊያ ግብ በ40ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

በሌላ ጨዋታ ይርጋለም ላይ ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን በሜዳው 3ለ1 በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መመለስ ችሏል።

ለጅማ አባጅፋር አዳማ ሲሶኮ 28ኛ ደቂቃ፣ ኦኪኪ አፎላቢ 39ኛ ደቂቃ እና ሄኖክ ኢሳይያስ 63ኛ ደቂቃ ጎሎቹን ሲያስቆጥሩ የሲዳማ ቡናን የማስተዛዘኛ ግብ ይገዙ ቦጋለ በ77ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

በሜዳው አዳማ ከተማን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ለሀዋሳ ከተማን የማሸነፊያ ግቦች አዲስአለም ተስፋዬ በ6ኛ ደቂቃ እንዲሁም ዳዊት ፋቃዱና በ27ኛ ደቂቃ ሲያስቆጥሩ ለአደማ ከነማ ከመሸነፍ ያላዳነችውን ግብ ከነዓን ማርክነህ ማስቆጠር ችሏል።

የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ውጤት ተከትሎም ጅማ አባ ጅፋር በ35 ነጥብ ፕሪምየር ሊጉን መምራት ጀምሯል።

ደደቢት በ33 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ በእኩል 32 ነጥብ በግብ ተበላልጠው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የአምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀሪ ጨዋታዎች እያሉት በ30 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ድሬደዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በእኩል 18 ነጥብ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ17 ነጥብ ከ14 እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።