47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ስታዲየም መዛሬው እለት መካሄድ ጀምሯል።

በዛሬው እለት ከማለዳው 2 ሰዓት ጀምሮ በድምቀት እየተካሄደ ያለው ሻምፒዎናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 14 ድረስ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆይ ነው።

በሻምፒዮናው ላይም 40 ክለቦችና ተቋማት እንዲሁም ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 500 ሴት እና 737 ወንድ በድምሩ 1 ሺህ 237 አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።

በዛሬው እለትም የአሎሎ ውርወራ ሴቶችና ወንዶች፣ የሱሉስ ዝላይ ወንዶች ፍፃሜያቸውን የሚያገኙ ይሆናሉ፡፡

ሰባት ውድድሮችም ማጣሪያ ይደረግባቸዋል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት የሚሰጣቸው ሲሆን፥ ክብረ ወሰን የሚያሻሽሉ አትሌቶች ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት እንደሚያገኙ ተጠቁሟል።

በውድድሩ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶች በሐምሌ ወር በሚከናወነው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ተነግሯል ።

በሻምፒዮናው ላይ አትሌቶቹ የሚያስመዘገቡት ውጤት በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እውቅና እንደሚያገኝም ተገልጿል።

ሻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ተነግሯል።

ይህ ውድድር ክለቦች በዓመቱ ያገኙትን ነጥብ የሚያሻሽል በመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖረው ተነግሯል።