47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማክሰኞ ይጀመራል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 6፣ 2010፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ይህ ሀገር አቀፍ ሻምፒዎና ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፥ ሚያዚያ 9 እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2010 ዓ ም እንደሚከናወን ታውቋል።

በሻምፒዮናው የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶች በሐምሌ ወር በሚከናወነው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ተናግሯል ።

በዚህ ውድድር 40 ክለቦችና ተቋማት እንዲሁም ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 500 ሴት እና 737 ወንድ በድምሩ 1ሺህ237 አትሌቶች የሚካፈሉበት ይሆናል።

በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት የሚሰጣቸው ሲሆን፥ ክብረ ወሰን የሚያሻሽሉ አትሌቶች ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት እንደሚያገኙ ተጠቁሟል።

በሻምፒዮናው ላይ አትሌቶቹ የሚያስመዘገቡት ውጤት በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር እውቅና እንደሚያገኝም ተገልጿል።

ሻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ተነግሯል።

ይህ ውድድር ክለቦች በዓመቱ ያገኙትን ነጥብ የሚያሻሽል በመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖረው ተነግሯል።

ምንጭ፦ ኢዜአ