በፕሪምየር ሊጉ ሀዋሳ ከተማና ወላይታ ድቻ አቻ ተለያይተዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ ዛሬ ሶዶ ላይ ተካሂዷል።

የ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ ቀሪ ጨዋታው ወላይታ ድቻን ከሀዋሳ ከተማ ነው ያገናኘው።

ጨዋታውም 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ሁለቱም ክለቦች ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።

በጨዋታው ላይ ጃኮ አራፋት የወላይታ ብቸኛ ጎል ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ያስቆጠረ ሲሆን፥ የወላይታ ድቻው ሙባረክ ሽኩር በ60ኛው ደቂቃ ላይ በራሱ ጎል ላይ ያስቆጠራት ጎል ሀዋሳን አቻ አድርጋለች።

ጨዋታው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም ሁኔታው ተረጋግቶ ተጠናቋል።

የ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ጨዋታዎች በትናንትናው እለት ተካሂደዋል።

አዲስ አበባ ላይ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ደደቢት ጨዋታውን ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት አጠናቋል።

ክልል ላይ በሜዳው መከላከያን ያስተናገደው አዳማ በከነዓን ማርክነህ ጎል 1ለ0 አሸንፎ ወጥቷል።

በሌሎች ጨዋታዎች ጅማ ላይ መቐለ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል።

አርባ ምንጭ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው አርባ ምንጭ ከተማ 2 ለ 0 ሲያሸንፍ፥ አዲግራት ላይ ወልዋሎ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አቻ ተለያይተዋል።

ወልዲያ ላይ ወልዲያ ከተማን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው ጨዋታ 90ኛው ደቂቃ ላይ በተፈጠረ ረብሻ ተቋርጧል።