የወልዲያ ከተማና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በተፈጠረ ረብሻ ተቋረጠ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ወልዲያ ላይ ወልዲያ ከተማ ከፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ በተፈጠረ ረብሻ አማካኝነት ተቋረጠ።

እስከ 90ኛው ደቂቃ ድረስ በመልካም ድባብ 1 ለ 1 ዘልቆ የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት ማግኘት የቻሉት አፄዎቹ በከድር ኸይረዲን አማካኝነት መሪ መሆን ችለው ነበር።

ሆኖም ይህች ጎል በተቆጠረች ቅፅበት ደጋፊዎች ሙሉ የሜዳውን ክፍል በመውረር ዳኞች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

በረብሻው ምክንያትም የጨዋታው ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ እና ረዳቱ ሙስጠፋ መኪ ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ለህክምና በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ማምራታቸው ተነግሯል።

በተጨማሪም የወልዲያ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስም በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ራሳቸውን እስከመሳት ደርሰው ሆስፒታል ይገኛሉ ተብሏል።

ጨዋታውም በሜዳ ላይ በተከሰተ ችግር ምክንያት በጭማሪ ሰዓት ላይ በፋሲል ከነማ 2-1 መሪነት ሊቋረጥ ችሏል።

በቀጣይ የጨዋታውን መቋረጥ እና ያስከተለውን ጉዳት አስመልክቶ የጨዋታው ኮሚሽነር ስንታየሁ እድሉ የሚያቀርቡት ሪፖርት የሚጠበቅ ይሆናል።

 

 

ምንጭ፦ ሶከር ኢትዮጵያ