ለወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድንና ተጨዋቾች ከደጋፊዎች 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተበረከተ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)የወላይታ ድቻ እግር ኳስ ቡድን ሰሞኑን የግብፁን ዛማሊክ ቡድን ማሸነፉን ተከትሎ ከደጋፊዎቹ 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደረገለት።

ደጋፊዎቹ ካበረከቱት ገንዘብ ውስጥ 6 ነጥበ 5 ሚሊየኑ ለቡድኑ ማጠናከሪያና ግማሽ ሚሊየን ብሩ ለተጫዋቾቹ ሽልማት የሚበረከት ነው።

በተጨማሪም ክለቡ ከራሱ ወጭ በማድረግ ለ30 ተጫዋቾችና የልኡካን ቡድን አባላት 600 ሺህ ብር ሽልማት መመደቡን የቡድኑ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጌታሁን ጋረደው አስታውቀዋል።

ቡድኑ በዛማሊክ ላይ የተቀዳጀው ድል የሀገሪቱ ህዝቦች መካከል የበለጠ መቀራረብና አንድነትን ለመፍጠር አሰተዋፅኦ ማደረጉን ተናግረዋል።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ በበኩላቸው፥ “በጥቂት ጊዜ በተሰራ ስራ የመጣው ውጤት የቡድኑን እቅም የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜ ድክመታችን በማረም ለተሻለ ድል እንሰራለን” ብለዋል።

ቡድኑ ትላንት ወላይታ ሶዶ ከተማ ሲገባ በህዝቡና በከተማው አሰተዳደር ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

የግብጹን ሃያል ክለብ ዛማሌክን በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር የተቀላቀለው ወላይታ ድቻ ትላንት ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር መደልደሉ ይታወሳል።

በዚህም ድቻ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ ሲጫወት የመልስ ጨዋታውን ደግሞ በሜዳው የሚያደርግ ይሆናል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ