በ17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤት ላስመዘገበው ቡድን የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በበርኒንግሃም በተካሄደው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ በድል ለተመለሰው የአትሌቲክስ ልኡካን ቡድን የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ።

የማበረታቻ ሽልማቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ናቸው በትናንትናው እለት ያበረከቱት።

በዚህም በ17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከአለም 2ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ በ1ኛነት ውድድሩን አጠናቆ ለተመለሰው የልኡካን ቡድን ወደ 300 ሺህ ብር ገደማ የሚጠጋ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።

በሥነ ስርአቱ ወቅት የወጣቶች እና ስፖርት ሚንስትር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ተገኝተዋል።

የክብር እንግዶቹ፥ በ17ኛው የአለም የቤት ውስጥ ውድድር የተገኘው ከፍተኛ ውጤት እንድንኩራራ የሚያደርግ ሳይሆን እንደሃገር አሁንም ተፎካካሪዎቻችንን በከፍተኛ ሁኔታ በልጠን ለመገኘት ጠንክረን መስራት እንዳለብ ያመላከተ ነው ብለዋል።

በተያያዘ ቅዳሜ መጋቢት 8 2010 ዓ.ም በአልጀሪያ ክሌፍ ከተማ በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከእስከዛሬዎቹ የአፍሪካ አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች በላቀ ሁኔታ 2 ወርቅ፣ 4 ብር፣ 2 ነሃስና 5 ዋንጫ በማግኘት ከአፍሪካ 2ኛ ሆና በከፍተኛ ውጤት ውድድሯን አጠናቅቃለች።

ቡድኑም በሁለት ምድብ ወደ ሃገሩ በመመለስ ላይ ሲሆን፥ የመጀመሪው ምድብ እሁድ ለሊት አዲስ አበባ ገብቷል፤ ሁለተኛው ቡድንም ሰኞ ለሊት አዲስ አበባ እንደሚገባ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።