የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2ኛው ዙር ጨዋታ በ1 ሳምንት ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ጨዋታ መርሀ ግብር በአንድ ሳምንት እንዲራዘም ተወሰነ።

የመርሀ ግብሩ መራዘም የተገለጸው ዛሬ የሊጉ ክለቦች የአንደኛ ዙር የውድድር አፈፃፀም ሲገመገም ነው።

በዚህም ለፕሮግራሙ መራዘም በምክንያትነት የቀረበው ክለቦች “ለእረፍትና ለሁለተኛው ዙር የውድድር ዝግጅት በቂ ጊዜ አላገኘንም” በማለታቸው መሆኑ ተገልጿል።

ውድድሩ መጋቢት 8 እና 9 እንደሚጀመር ቀደም ብሎ ቢገለፅም በተደረገው ማሻሻያ ጨዋታዎቹ መጋቢት 15 እና 16 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት እንዲካሄዱ ነው የተወሰነው።

የ2010 የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ፥ ሊጉን ደደቢት በ29 ነጥብ ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ ጅማ አባ ጅፋርና መቐለ ከተማ በተመሳሳይ በ25 ነጥብ በጎል ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።

የከፍተኛ ጎል አግቢነትን ኦኪኪ አፎላቢ ከጅማ አባ ጅፋር እንዲሁም ጌታነህ ከበደ ከደደቢት በተመሳሳይ በዘጠኝ ጎል እየመሩ የመጀመሪያው ዙር የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠናቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ