የዓለም ዋንጫ ዛሬ አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ዋንጫን ዛሬ ከካርቱም ወደ አዲስ አበባ ገብቷል። በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

በአቀባበል ስነ ስርዓቱም ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ከሰዓት በኋላም በቤተ መንግስት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት የአቀባበል ዝግጅት ተደርጎለታል።

የፊፋ ተወካዮችም ዋንጫውን ለፕሬዚዳንቱ በማስረከብ የአለም ዋንጫ በይፋ መግባቱ ተበስሯል።

በ2018 በሩሲያ የሚካሄደውን የአለም ዋንጫ በማስመልከት 50 ሃገራትን ለመዞር ያቀደው ይህ ዋንጫ በአፍሪካ 10 ሃገራትን እንደሚጎበኝ የፊፋ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 126 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጉዞ እንደሚያደርግ ነው የተመለከተው።

የአለም ዋንጫው ከስምንት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ መምጣቱ የሚታወስ ሲሆን፥ የዛሬው ሁለተኛው ጉብኝቱ ነው።


በአብረሃም ፈቀደ