በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ወላይታ ዲቻ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 14 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ኢትዮጵያን የወከለው ወላይታ ዲቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋገጠ።

ዛሬ በሃዋሳ አለም አቀፍ ስታዲየም የመልስ ጨዋታቸውን ያደረጉት ወላይታ ዲቻዎች የዛንዚባሩ ዚማሞቶን በማሸነፍ ነው ወደቀጣዩ ዙር ያለፉት።

በዛሬው ጨዋታ ወላይታ ዲቻዎች 1 ለ 0 ሲያሸንፉ ጃኮ አረፋት በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ጎሏን አስቆጥሯል።

ዛንዚባር ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል፤ በደርሶ መልስ ውጤትም 2 ለ 1 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል።

ወላይታ ዲቻ በቀጣዩ ዙር ከግብጹ ሃያል ክለብ ዛማሌክ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።