ኢትዮጵያ 16ኛውን የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በ13 ሜዳሊያዎች 2ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቀቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በ13 ሜዳሊያ 2ኛ ሆና ውድድሩን አጠናቃለች።

ከየካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሩዋንዳ ኪጋሊ ሲካሄድ የነበረው የብስክሌት ውድድር በትናንትናው እለት ፍጻሜውን አግኝቷል።

ኢትዮጵያም በውድድሩ 3 ወርቅ፣ 7 የብር እና 3 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 13 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከኤርትራ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ሶስቱም የወርቅ ሜዳሊያዎች የተገኙት በሴት የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ሲሆን፥ ሰላም አምሀ በታዳጊ ሴቶች፣ በቡድን በአዋቂ ሴቶች የግል የሰአት ሙከራ፣ እንዲሁም በቡድን ከ23 ዓመት በታች ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ተገኝቷል።

ኤርትራ በ10 ወርቅ በ5 ብር እና 5 ነሐስ በድምሩ 20 ሜዳሊያዎችን በማግኘት የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ስትሆን፤ አስተናጋጇ ሩዋንዳ በ3 ወርቅ፣4 ብር እና 3 ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎች ሶስተኛ ወጥታለች።

ብሩንዲ 1 የብር ሜዳሊያ፣ ናሚቢያ 1 የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት በቅደም ተከተል አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ