በሩዋንዳ በሚካሄደው የአፍሪካ ብስክሌት ውድድር ላይ ኢትዮጵያ 14 ብስክሌተኞችን ታሳትፋለች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩዋንዳ በሚካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ብስክሌተኞች የፊታችን ሰኞ ወደ ኪጋሉ ያቀናሉ።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው መኮንን እንደገለጹት፥ በውድድሩ ላይ በወንዶች ስምንት በሴቶች ስድስት በአጠቃላይ 14 ብስክሌተኞች ይሳተፋሉ።

በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ከየካቲት 6 እስከ 11 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ 18 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን የፊታችን ሰኞ ወደ ስፍራው ያመራል።

ተወዳዳሪዎቹ ከጉና፣ መሶቦ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል እና ከትራንስ የብስክሌት ክለቦች መመረጣቸውንና ብስክሌተኞቹ በአዋቂዎች እና በወጣቶች ምድብ ተከፍለው እንደሚወዳደሩ አቶ ግዛቸው ገልፀዋል።

በተያዘው ዓመት በአፍሪካ በተደረጉ የብስክሌት የቱር ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ ተወዳዳሪዎችና ባለፈው ዓመት በግብፅ የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተሳታፊዎች በሩዋንዳው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ብስክሌተኞችን ለመምረጥ ዋነኛ መመዘኛ ነበር።

በተጨማሪም በቅርቡ በስዊዘርላንድና ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት(ዩሲአይ) በሰጠው ስልጠና የተሳተፉ ብስክሌተኞችና በዓለም አቀፍ የብስክሌት ቡድኖች ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ተወዳዳሪዎች በልዑካን ቡድኑ ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል።

ከተወዳዳሪዎቹ መካከልም በዚሁ ዘርፍ ከሁለት ዓመት በፊት በሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው ፅጋቡ ገብረማርያም በዋንኛነት እንደሚጠቀስ ነው አቶ ግዛቸው ያስረዱት።

ፅጋቡ ከሶስት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና በግል በተካሄደው ውድድር አንደኛ መውጣቱ ይታወሳል።

በወንዶች ፍስሀ ገብረዮሃንስ፣ ክፍሎም ገብረመድህን እና ታምራት መረሳ፤ በሴቶች እየሩሳሌም ዲኖ፣ ሰላም አምሀና ፀጋ ገብሬ ከተሳታፊዎቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት ግብፅ በተደረገው 15ኛ የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ እንደተገኘ ያስታወሱት አቶ ግዛቸው፥ በዘንድሮው ውድድር የተሻለ የሜዳሊያ ቁጥር ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት ከተደረጉ የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናዎች ከተወዳዳሩ ብስክሌተኞች የዘንድሮው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች የተሻለ ልምድና ዓለም አቀፍ የውድድር ተሞክሮ እንዳላቸው ነው አቶ ግዛቸው ያብራሩት።

ከብስክሌተኞቹ በተጨማሪ ሁለት አሰልጣኞች፣ አንድ መካኒክና አንድ የህክምና ባለሙያ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ መካተታቸውን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም የሚካሄደውን 17ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ለማዘጋጀት ለአፍሪካ የብስክሌት ህብረት (ካክ) ጥያቄ ማቅረቧን ጠቁመዋል።

ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ሌሎች አገሮች ለህብረቱ ጥያቄ ማቅረባቸውንና የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በሚካሄደው የህብረቱ መደበኛ ስብስባ ውድድሩን የሚያዘጋጀው አገር በይፋ እንደሚታወቅ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ከተመረጠች ብዙ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን በተሻለ መልኩ ለማሳተፍ እንደሚረዳና ለአገር ገጽታ ግንባታ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች የብስክሌት ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም በቱር ሴኔጋል ውድድር ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞችን ለማሳተፍ እቅድ መያዙን አስታውቀዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ