በፕሪሚየር ሊጉ መቐለ ከተማና አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉት ሶስት ጨዋታዎች የተጀመረው የሊጉ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ እና አርባምንጭ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል።

በዚህም በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ የተመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቐለ ከተማ ጨዋታ በመቐለ ከተማ 2 ለ1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

መቐለ ከተማ አማኑኤል ገብረሚካኤል ጨዋታው በተጀመረ በ32ኛው ደቂቃ በተገኘ ፍፁም ቅጣት እና ከእረፈት በኋላ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ነው ኢትዮ ኤሌክትሪክን መርታት የቻለው።

ተክሉ ተስፋዬ ደግሞ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የማስተዛዘኛዋን ግብ በ37ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

በዚህም የሁለት ጊዜ ሻምፒዮኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዘጠኝ ነጥቦች መጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በአንፃሩ ከስድስተኛው ሳምንት በኋላ ሽንፈት ያልገጠመው መቐለ ከተማ ዛሬ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ያስመዘገበው ድል በዋንጫ ፉክክር ውስጥ አስገብቶታል።

ይህም ክለቡ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፋ ነጥቡን 24 በማድረስ ከደደቢት በአንድ ነጥብ አንሶ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።

በሌላ በኩል አርባ ምንጭ ከተማ ከድሬደዋ ከተማ ዛሬ ያደረጉት ጨዋታ፥ ሁለት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን እርስ በእርስ ያገናኘ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአርባ ምንጭ ስታዲየም ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በዚህም በፌደራል ዳኛ ሚካኤል አረአያ የመሀል ዳኝነት የተደረገው ይህ ጨዋታ፥ አርባምንጭ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ0 በማሸነፍ ተጠናቋል።

በአጠቃላይ ፕሪሚየር ሊጉን ደደቢት በ25 ነጥብ ሲመራ መቐለ ከተማ በ24 ነጥብ ይከተሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 21 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

 

 

 

 

ምንጭ፦www.soccerethiopia.net