በሙምባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ በተካሄደ የታታ ሙምባይ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ድል ቀንቷቸዋል።

በወንዶቹ ሰለሞን ዴክሲሳ ሲያሸንፍ ርቀቱን 2 ሰዓት ከ09 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ በሆነ ጊዜ መጨረስ ችሏል።

ሌላው የሃገሩ ልጅ ሹመት አካልነው ደግሞ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በመጨረስ ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል።

ኬንያዊው ጆሹዋ ኪፕኮሪር ሶስተኛ በመሆን ጨርሷል።

በሴቶቹ ደግሞ አማነ ጎበና አሸናፊ ስትሆን 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ የገባችበት ጊዜ ነው።

የአምናዋ የውድድሩ አሸናፊ ቦርነስ ኪቱር ደግሞ በ2 ሰዓት ከ28 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሹኮ ገነሞ በ2 ሰዓት ከ29 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በመግባት የነሃስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናለች።

በሁለቱም ጾታዎች አሸፈፊ የሆኑ አትሌቶች 42 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል።


ምንጭ፦ iaaf.org/