በፕሪሚየር ሊጉ አርባ ምንጭና ጅማ አባ ጅፋር ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) 12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ዛሬ ሶስት ጨዋታዎችን አስተናግዷል።

አርባ ምንጭ ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው አርባ ምንጭ ከተማ 1 ለ 0 አሸንፏል።

የድል ጎሉን ፀጋዬ አበራ ማስቆጠር ችሏል።

ጅማ ላይ የተደረገው የጅማ አባ ጅፋርና የወልዲያ ጨዋታ ደግሞ፥ በጅማ አባ ጅፋር 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የማሸነፊያ ጎሉን ደግሞ አፎላቢ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።

በሜዳው ወላይታ ድቻን ያስተናገደው አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ጨዋታውን በአቻ ውጤት አጠናቋል።

እሸቱ መና እንግዳውን ቡድን መሪ ማድረግ ቢችልም፥ ሙሉዓለም ጥላሁን በመጀመሪያው አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ አዲግራትን አቻ አድርጎ ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ሊጉ ነገም ሲቀጥል ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ፋሲል ከነማን ያስተናግዳል።

አዲስ አበባ ላይ ይደረጉ የነበሩ አራት ጨዋታዎች ደግሞ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘማቸው የሚታወስ ነው።

 

 

ምንጭ፦ ሶከር ኢትዮጵያ