ፊፋ በኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ቢሮ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 11 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) በኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ቢሮ ሊከፍት ነው።

በአዲስ አበባ ይከፈታል የተባለው ቢሮ የተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮ ነው።

ማስተባበሪያ ቢሮው የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ባለፈው መጋቢት ወር በካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በገቡት ቃል መሰረት የሚከፈት ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በትዊተር ገጻቸው፥ ለቢሮው የሚሆነውን ቦታ የሚመለከቱ የፊፋ ተወካዮች በዛሬው እለት አዲስ አበባ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

በነገው እለትም ለቢሮው የሚሆን ቦታ ከመረጡ በኋላ ሪፖርት ያደርጋሉ ነው የተባለው።

ፌዴሬሽኑም ለማስተባበሪያ ቢሮው የሚሆን ቦታ እየመረጠ ነው ተብሏል።

ፊፋ በሴኔጋልና ደቡብ አፍሪካ ሁለት የማስተባበሪያ ቢሮዎች አሉት።