ብራዚላዊው ኮከብ ሮናልዲንሆ ከእግር ኳስ ጨዋታ ራሱን አገለለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብራዚላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ርናልዲንሆ የእግር ኳስ ጨዋታን በይፋ ማቆሙ ተገለፀ።

ከሀገሩ ብራዚል ጋር የዓለም ዋንጫን ያነሳው ሮናልዲንሆ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 ወዲህ የእግር ኳስ ጨዋታ አድርጎ አያውቅም።

የ37 ዓመቱ ሮናልዲንሆ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2002 የዓለም ዋንጫን ያነሳው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው።

እንዲሁም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2006 የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ከባርሴሎና ጋር ያነሳ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2005 ደግሞ የዓለም ኮከብ ተጫዋች ተብሎ በባላድኦር ተሸላሚ መሆን ችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የፈረንጆቹ 2004፣ 2005 የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እና በፈረንጆቹ 2006 የአውሮፓ ክለቦች የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል።

ወንድሙ እና መኪሉ የሆነው ሮቤርቶ አሲስ፥ ሮናልዲንሆ የእግር ኳስ ጨዋታን ሙሉ በሙሉ ማቆሙን በትናንትናው እለት አረጋግጧል።

ለእግር ኳሱ ኮከብ በብራዚል፣ በአውሮፓ እና በእሲያ የመሸኛ ስነ ስርዓት ለማዘጋጀት እየሰራን ነው ያለው ወኪሉ፥ ከብራዚል ብሄራዊ ቡድን ጋር በመሆንም ልዩ የሆነ ነገር ለማዘጋጀት አስበናል ብሏል።

ሮናልዲኒሆ የእግር ኳስ ጨዋታን በብራዚሉ ጀርሚዮ የጀመረ ሲሆን፥ በፈረንጆቹ 2011 ወደ ፈረንሳዩ ፒ.ኤስ.ጂ በዝውውር እስኪሄድ ድረስም በጀርሚዮ ሲጫወት ቆይቷል።

በስፔኑ ባርሴሎና ለ5 ዓመታት በነበረው ቆይታም 2 የላሊጋ ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለ ሲሆን፥ ወደ ጣሊያኑ ኤ.ሲ ሚላን በማቅናትም የፈረንጆቹ 2010-11 የሴሪ አ ዋንጫን ማንሳት ችሏል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ