የማራቶን ሯጩ አትሌት ኃይሌ ቶሎሳ በተከለከለ አበረታች መድሃኒት ሳቢያ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማራቶን ሯጩ አትሌት ኃይሌ ቶሎሳ ቦኩማ የተከለከለ የስፖርት አበረታች መድሃኒት ተጠቅሞ በመገኘቱ የቅጣው ውሳኔ ተላለፈበት።

የቅጣት ውሳኔውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ነው ያሳለፈበት።

አለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በአውሮፓውያኑ ግንቦት 15 ቀን 2016 በፔሩ በተካሄደው የሞቪስታር ሊማ ማራቶን ውድድር ላይ አትሌት ኃይሌ ቶሎሳ የስፖርት የፀረ-አበረታች መድሃኒት (ዶፒንግ) የህግ ጥሰት መፈፀሙን በመግለፅ እርምጃ እንዲወሰድበት ማሳወቁን ተከትሎ ነው ውሳኔው የተላለፈበት ተብሏል።

በወቅቱ በተደረገው የቤተ ሙከራ ምርመራ አትሌት ኃይሌ ቤንዞላይክጎኒን፣ ሜታሊክጎኒን እና ኮኬይን ሜታቦሊቲስ የተባሉ የተከለከሉ ቅመሞችን መጠቀሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤትም አለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የላከውን መረጃና የውሳኔ ኃሳብ መነሻ በማድረግ አትሌቱ ለ4 ዓመታት ከስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይሳተፍ ቅጣት አሳልፎበታል።

በዚህ መሰረት አትሌቱ የህግ ጥሰቱን መፈፀሙ ላይ የማጣራት ሂደት ከተጀመረበት የአውሮፓውያኑ ከግንቦት 15 ቀን 2016 ጀምሮ እስከ ግንቦት 15 ቀን 2020 በማንኛውም ሀገር አቀፍም ሆነ አለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የማይሳተፍ ይሆናል።

በቀጣይም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የፀረ አበረታች መድሃኒት እንቅስቃሴ በተለይም የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ፅህፈት ቤቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ፅህፈት ቤት በሀገር አቀፍ ደረጃ በውድድር ጊዜና ከውድድር ውጭ የስፖርተኞች የአበረታች መድሃኒቶች ወይም ዶፒንግ ምርመራ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ጽህፈት ቤቱ እስካሁን በአትሌቲክስ፣ በእግር ኳስ፣ በብስክሌት፣ በቦክስ እና በፓራኦሊምፒክ ስፖርቶች፥ በድምሩ ከ624 በላይ የሽንትና የደም ምርመራዎች ማድረጉን ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።